ሥልጣንን በማስመሰል

Views: 255

በመንግሥት ተቋማት በብዛት የሚሰማው ‹የአቅም ግንባታ› ጉዳይን ያነሱት ሙሉጌታ አያሌው (ዶ/ር) አቅምን እገነባለሁ በሚል ተቋማት ከአቅማቸው በላይ እቅዶችን እንደሚያቅዱ ይጠቅሳሉ። ይህ የማይፈጽሙትን እቅድ ማቀዳቸውና የማይችሉትን መሸከማቸው ሊሰብራቸው ሲገባ፣ የሆነው ግን ያ አይደለም። ለዚህ ደግሞ እያስመሰሉ መቆየታቸው እንደሚረዳቸው ነው ጸሐፊው የሚጠቅሱት። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የሚገኙ መንግሥታት፣ በተግባር የታየ ነገር ሳይሠሩ በማስመሰል ብቻ እንዴት ሥልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩም በማሳያ አስቀምጠዋል።

የአቅም ግንባታ
የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ወቅት የአቅም ግንባታ ስታራቴጂ ካወጣ በኋላ ስትራቴጂውን የሚያስፈፅም የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የሚባል አቋቁሞ ነበር። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ወይም ሚኒስቴር ካለው ለምን ሌላ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የሚባል አስፈለገው? አላውቅም። በእርግጥ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሲሠራ የነበረው የመንግሥትን አቅም መገንባት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአገሪቱን ከሆነ፤ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መኖሩ ችግር የለውም። በኋላ ይሄም ሚኒስቴር ታጥፎ ፕሮግራሞቹ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተበትነዋል።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ እቅድና በጀት ውስጥ የማይጠፋ አንድ ጉዳይ ነው፤ የአቅም ግንባታ። ለዚህ ተብሎ ብዙ በጀት ይያዛል። የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አገራትና ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይሰጣሉ። ብዙ ስብሰባዎች፥ ሥልጠናዎች፥ የውጭ ጉዞዎች ይከወናሉ፤ አቅም ለመገንባት። ሠራተኞቻቸውንና አመራሮችን ያስተምሩና ያስመርቃሉ፤ የመሥሪያ ቤቱን አቅም ለመገንባት።
የአቅም ግንባታ ጉዳይን ያነሳሁት፤ የአቅም ግንባታን የሚመለከት አንድ መጽሐፍ ሳነብ ያገኘሁትን አንድ ሐሳብ ለማካፈል ፈልጌ ነው። የመጽሐፉ ደራሲያን በጉዳዩ ላይ በተለያዩ አገራት ጥናትና የማማከር ሥራዎችን ሠርተዋል።

ብዙ የድሃ አገራት መንግሥታት እጅግ በጣም የተለጠጠ የእድገት እቅድ ያወጣሉ። እቅዱን ባወጡበት ወቅት ካላቸው የመፈፀም አቅም አኳያ ካየነው፤ እቅዱ ፈፅሞ የሚሳካ አይደለም። ነገር ግን እነዚህ መንግሥታት አብረው የአቅም ግንባታ እቅድም ያዘጋጃሉ። ስለዚህ ሐሳቡ፤ አሁን ያለንን አቅም አሳድገን ይሄን የተለጠጠ እቅድ እናሳካለን የሚል ነው።

የመጽሐፉ ደራሲዎች እንደሚሉት፣ የእነዚህ መንግሥታት የአቅም ግንባታ እቅድም የተለጠጠ ነው፤ የሚሳካ አይደለም። የተለያዩ አገራትን ታሪካዊ የአቅም ልክ የሚያሳይ መረጃ ወስደው፤ በአማካኝ አንድ አገር አቅሙን ካለበት ደረጃ አንድ ወደላይ ከፍ ለማድረግ ምን ያህል ዓመታት እንደወሰዱበት ተመለከቱ። ከአርባ ዓመታት በላይ። ልብ በሉ፤ እመርታዊ የአቅም ለውጥ ለማምጣት አይደለም። አንድ ደረጃ ወደላይ ከፍ ለማለት ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ከተመለከትነው፤ የአምስት ዓመት የተለጠጠ አቅምን፤ በእነዚያው ዓመታት ውስጥ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በመሥራት፤ ማሳካት አይቻልም።

ችግሩ መሳካት አለመቻሉ አይደለም። ጸሐፊዎቹ እንደሚሉት፤ ‹ራስ ሳይጠና ጉተና› ነው። ጉልበት ከሚሸከመው በላይ በመጫን መፈተሽ ብቻ ሳይሆን ማጠንከር ይቻላል። በየጊዜው ከተፈተሸ፥ ከተፈተነ፤ እየጠነከረ ይሄዳል። ነገር ግን የምትጭነው ነገር ልክ ሊኖረው ይገባል። ያለዚያ ሰብሮ ሊጥለው ይችላል።

ለመኖር ማስመሰል
ታዲያ እነዚህ መንግሥታት እንዴት አልተሰበሩም? እንዴትስ በተከታታይ እንሠራዋለን ያሉትን ነገር ሳይሠሩ፤ ሥልጣናቸውን ይዘው ሊቀጥሉ ቻሉ? መልሱን ፍለጋ ወደ እንሰሳትና ባህሪዎቻቸው ሄዱ፣ ደራስያኑ። በዱር ከሚኖሩ እንሰሳት አንዳንዶቹ በአቅማቸው ታፍረውና ተከብረው ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ አንዳንድ እባቦች እጅግ መርዛማ ናቸው። በመርዛቸው ታፍረውና ተከብረው ይኖራሉ። አንዳንዶቹ በመሮጥ አቅማቸው ከአደጋ በማምለጥ ይኖራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸውን ከከባቢው ጋር በማመሳሰል።

ከእነዚህ የሚለዩና የተለየ እቅድ የሚከተሉ እንሰሳትም አሉ። ይሄ ስልት የማስመሰል ስልት ይባላል። አቅሙ ባይኖራቸውም አቅሙ እንዳላቸው ያስመስላሉ። ስለዚህ በማስመሰል ታፍረውና ተከብረው ይኖራሉ። መርዛማ እባብ ባይኖራቸውም፤ በቀለምና በቅርፅ ተናዳፊዎቹን ይመስላሉ። አንዳንድ ቢራቢሮዎች ክንፎቻቸው ዐይን የሚመስሉ ነጠብጣቦች አሏቸው።

ስለዚህ እንደ ደራሲዎቹ እምነት፤ እነዚህ መንግሥታት ሳይፈፅሙ እየኖሩ ያሉት በማስመሰል ነው። የመፈፀም አቅም እንዳላቸውና ውጤት እንዳመጡ በማስመሰል ይኖራሉ። ችግሩ፤ በማስመሰል ዝንተ ዓለም አይኖርም። ማስመስል ዘላቂ እንዲሆን ኹለት ነገሮች መሟላት አለባቸው።

ዝግ ምህዳር
አንደኛው ቅድመ ሁኔታ፤ ምህዳሩ ዝግ መሆን አለበት። ማለትም ሥልጣን የያዘውን መንግሥት ሊያሳጣ የሚችል ሌላ አካል መኖር የለበትም። ከዚህ ቅድመ ሁኔታ አኳያ የኛን አገር መንግሥት ልንገመግመው እንችላለን። ምህዳሩ ለማንና በምን ያህል ዝግ ነበር? መንግሥትን የሚያሳጡ የሚባሉ አካላት መካከል የግል ዘርፉና የሲቪል ማኅበረሰቡ ናቸው። ለእነዚህስ ምህዳሩ ምን ያህል ክፍት ነበር?

የምህዳር መዘጋትን አስመልክቶ ከዚህ በፊት ስለ ጫት የጻፍኩት ነገር ነበር።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እንደ ጫት የተሳካለት የግብርና ምርት የለም። ያልደረሰበት ቦታ የለም። ገበሬዎች ቡናቸውን ሁሉ ሳይቀር እየነቀሉ ጫት ተክለዋል። ጫት ግን፤ ከመንግሥት ምንም አይነት ድጋፍ አልተደረገለትም። የመስኖ ውሃ ወይም ምርጥ ዘር፣ የአረምና ተባይ ማጥፊያ ኬሚካል፣ የብድር አገልግሎት አልቀረበለትም። ሌላው ይቅር የጫት ገበሬዎች የአረንጓዴ ልማት ጀግኖች ተብለው አልተሸለሙም። ነገር ግን አብቧል። በአንፃሩ ለሌሎች የግብርና ምርቶች በመንግሥት ያልተደረገ ነገር የለም። ታዲያ፤ ጫት መንግሥትን እያሳጣው አይደለ!

መልክ ተኮር ግምገማ
ኹለተኛው ቅድመ ሁኔታ፤ እያሰመሰሉ ለመኖር፤ ከዝግ ምህዳር በተጨማሪ፤ በስርአቱ አዳዲስ ሐሳቦች የሚገመገሙበት ስልትን መመልከት ይገባል። ኹለት ዓይነት ግምገማዎችን በዋናነት ማሰብ ይቻላል።

አንደኛው ግምግማ ቅርፅ/መልክ ተኮር የሚባለው ነው። አንድ ሐሳብ ሲቀርብ፤ የምትንገመግመው ከምንፈልገው ቅርፅና መልክ ጋር፣ ምን ያህል ይመሳሰላል የሚለውን ነው። ብዙ የሕግ ባለሙያዎች የግምገማ ስልታቸው ይህ ነው። ይሄ ውል መፍረስ አለበት ወይም የለበትም ብለው ክርክር ሲያቀርቡ፤ ለምን ቢባሉ፤ የሚጠቅሱት የሕግ አንቀፅ ነው። ስለዚህ ግምገማቸው፤ አንድ ነገር ምን ያህል ከሕጉ ጋር የተስማማ ነው የሚል ነው። ችግር የለውም። ችግሩ፤ እነዚሁ ባለሙያዎች ሕግ አርቅቁ ሲባሉ፤ ከዚሁ መልክ ተኮር ግምገማ ካልወጡ ነው።

ኹለተኛው አይነት ግምገማ ፍሬ ተኮር ግምገማ ነው። በዚህ ዋናው ወሳኙ ጉዳይ፤ ለግምገማ የቀረበው ሐሳብ የምንፈልገው አይነት ፍሬ በበቂ ጥራትና መጠን ያፈራል ወይ ነው። የቻይናው መሪ ዴንግ እንደሚለው፤ ድመቷ ጥቁር ትሁን ነጭ ዋናው አይጥ መያዟ ነው።

መልክ ተኮር ግምገማ ለአስመሳዮች የተመቸ ነው። ትኩረትህ ፍሬ ላይ ስለማይሆን፤ ማንኛውም ሰው በመልክ እያታለለ ሊኖር ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ወግ አጥባቂ ነው። ተራማጅ አይደለም። እኔ ደግሞ ከዚህ በላይ ይሄዳል ባይ ነኝ፤ የኋልዮሽ።

ግምገማው በመልክ ሲሆን፤ ሰዎች ከሚገባው በላይ ጊዜያቸውን፥ ጉልበታቸውንና፥ አቅማቸውን ለመልክና ቅርፅ ያውሉታል። ቃላትን በማጥናት፣ ንግግርን በማሳመር።
ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው፤ እያስመሰሉ መዝለቅ የሚቻለው በኹለት ሁኔታዎች ነው። ምህዳሩ ዝግ ከሆነና ሰዎችና ሐሳቦች የሚገመገሙት መልክ/ቅርፅ ተኮር በሆነ ስልት ከሆነ ነው። በእርግጥም እነዚህ መንግሥታት፤ እንደ ደራሲዎቹ እምነት፤ ሳይፈፅሙ፥ ሳይሠሩ ነገር ግን በሥልጣን የዘለቁት በማስመሰል ስትራቴጂ ነው።

‹ኢሕአዴግ›ና መልክ ተኮር ግምገማው
የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣን በተቻለኝ በመደበኛነት አነባለሁ። በተለይ ድሮ ‹ጎሲፕ› አሁን ‹ፋይን ላይን› የሚባለውን አምድ። በአንድ ወቅት ስለኢሕአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ክርክር ጽፎ ነበር። ጉዳዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ይመለከታል። ከኮሚቴው አባላት ውስጥ የተወሰኑት የገንዘብ ችግር ስለገጠመንና ፈቃደኞች ስላገኘን፣ የተወሰኑትን ፓርኮች የውጭ ባለሃብቶች በራሳቸው ገንዘብ ገንብተው እያከራዩ ይጠቀሙ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል። ሐሳቡን የሚቃወሙት ሰዎችም ይሄማ ከመስመራችን እና ከመለስ ራእይ ጋር ስለሚፃረር አንቀበለውም እንዳሉ ዘግቧል።

ደነቀኝ። እታች ያለው ካድሬና ሥራ አስፈፃሚ መስመርንና የመለስን ራእይ ለግምገማ ዋነኛ መመዘኛ አድርጎ መውሰዱ ጥያቄ ያጭራል። እውን ይሄ ድርጅት ተራማጅና አብዮተኛ ነው?
በዚህ ሲገርመኝ፤ በቅርብ የታተመውን የኢሕአዴግ ቁልቁለት መጽሐፍ አነበብኩ። ቁርጤን ነገረኝ። ድርጅቱ በመልክ ተኮር ግምገማ ብቻ የተካነ ነው። አሁንም ሁሉም ንግግሮች በመስመር፥ በመለስ ራእይና በመሳሰሉ መልክ ተኮር ግምገማ የተሞሉ ናቸው።

መፍትሄን ፍለጋ ልማታዊ ወደሚባሉ አገራት መሄድ መልክ ተኮር ግምገማ ነው። እጅግ የሚደንቀው ደግሞ፤ ችግርህን ለማወቅ ልማታዊ ወደሚባሉ አገራት ሄደህ “ችግራችንን አውቀነዋል። ኮሪያም እንዲህ አድርጓት ነበር። የተሻላት ልማቷን በማፋጠኗ ነው። ስለዚህ መፍትሄው እኛም ልማታችንን ማፋጠን አለብን” ብለህ ስትናገር መስማት ነው።

ዋናው ነገር ድመቷ አይጥ መያዟ
ሁላችንም፥ ሁልጊዜ በፍሬ ተኮር ግምገማ ብንተጋ ተጠቃሚዎች አይደለንም። ነገር ግን ዋና ውሳኔ ሰጪዎች እኛ በመልክ ተኮር ግምገማ እንድንተጋ መልኩን የሚቀርፁት ግን፤ መካን ያለባቸው በፍሬ ተኮር ግምገማ ነው። ለዚህም የግልና ተቋማዊ አቅም ሊኖራቸው ይገባል።

መልክ ተኮር ግምገማ ሕይወትን ያቀላል። ምክንያቱም ፍሬ ተኮር ግምገማ ከፍተኛ የመረጃና የትንተና አቅም ስለሚጠይቅ። እነዚህን አቅሞች በየግለሰቦቹ ከመበተን በማእከል መጠቀም ይቀላል። በዚህ ግምገማ ውስጥ የሚደበቁት አስመሳዮች ብቻ አይደሉም። አስመሳዮች ማለት የግል ልዩ ግብ ያላቸው፥ ለዚህም አቅሙ ያላቸው፥ ነገር ግን ልዩ የግል ግባቸውን በግልፅ ማራመድ የማይደፍሩት ናቸው።
በመልክ ተኮር ግምገማ አቅመ ቢሶቹም ይደበቃሉ። አቅመቢሶቹ ድብቅ ዓላማ ሊኖራቸውም ላይኖራቸው ይችላል። ዋናው እርሱ አይደለም። አቅሙ የላቸውም። በፍሬ ተኮር ግምገማ ለመትጋት የትንተና አቅሙ የላቸውም።

ልብ በሉልኝ፤ በረከት ሰምኦን፤ በመጽሐፉ ኢሕአዴግ የሚታወቅበት ትልቁ አቅሙ የንድፈ ሐሳባዊና የትንተና አቅሙ እንደሆነ ይናገራል። በግልፅ ባይለውም፤ ስለ መለስ እየተናገር ይመስለኛል። በመጽሐፉና በሌሎች ንግግሮቹ ደግሞ ከመለስ ቀጥሎ የዚህ ንደፈ ሐሳባዊና የትንተና አቅም ባለቤት እርሱ ነው። የራሱን መጽሐፍ፥ ሌሎች ንግግሮቹን፥ እና የኢሕአዴግ ቁልቁለትን ስመለከት ደግሞ፤ እርሱም ሆነ ሌሎቹ የተካኑት በመልክ ተኮር ግምገማ ነው። የእርሱን መጽሐፍ ሳነበው ደግሞ የኢኮኖሚክስ መሰረታዊ ከሚባሉ ሐሳቦች ምን ያህል በሙግት ሳይሆን በዝምታ እንደተጣላ ነው።
በመልክ ተኮር ግምገማ፤ አቅመ ቢሱም ባለ ክፉ ልቡም ይደበቅበታል። ድርጅቱ ከሥራ አስፈፃሚው እስከ ፍሮንት ላይኑ ካድሬ ጭምር በዚህ አይነት መልክ ተኮር ግምገማ መትጋቱ አስገራሚ ነው። ለዚህ እኮ ነው፤ ከመጀመሪያውኑ እነዚህ አዲስ ቃላት ሲመጡ፥ አላማቸው ምንድን ነው ብለን መጠየቅ ያለብን። ከማስመሰል ውጭ፥ ለአቅመ ቢሱም ሆነ ለባለ ክፉ ልቡ መደበቂያ የሚሆኑ ቃላት ናቸው። “መደመርስ” እንዴት ነው በተለያዩ ግልፅ መልኮች ወደ ታች የሚወርደው። ወደፊት እናየዋለን፤ ጊዜ ከሰጠን።
ጸሐፊው የተለያዩ ሐሳቦችን በቋሚነት በፌስቡክ ገጻቸው @insights.of.jaaj ያካፍላሉ

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com