ያልተቋጨው የመስቀል አደባባይ ውዝግብ እና መፍትሔው

0
1422

አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው መስቀል አደባባይ፣ ዓመቱን ጠብቆ የመስቀል በዓል የሚከበርበት፣ የመንግሥት ትላልቅ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት፣ የተለያዩ የሙዚቃ ትዕይንቶች በየወቅቱ የሚቀርቡበት የከተማዋ ስመጥር ቦታ ነው።
ይህ ቦታ በመንግሥትና በኃይማኖት ተቋማት መካከል በየወቅቱ የይገባኛል ጭቅጭቅና ውዝግብ ሲያስነሳ ቢስተዋልም፣ ችግሩ እስካሁን ሊቀረፍ ባለመቻሉ አለመግባባቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ እንጂ ሲቀንስ እየተስተዋለ አይደለም።

በዚህም፣ ከሰሞኑ የፕሮቴስታንት የዕምነት ተቋማት በቦታው ላይ መርሃ ግብር ለማካሄድ ባደረጉት እንቅስቃሴ መነሻነት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያንና በመንግሥት መካካል የተነሳው አለመግባባት ለጉዳዩ ዕልባት አለመቸሩን በማያሻማ መልኩ የሚያስረዳ ነው።
ባሳለፍነው የጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት፣ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች በአደባባዩ ያቀዱትን ዝግጀት በሚያካሂዱበት ወቅት፣ ባለይዞታው ሳይፈቅድ መንግሥት ለምን ፈቀደ በሚል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ እንደተገባና አካባቢው ላይም የሠላም መደፍረስ ተፈጥሮ እንደነበር የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ‹‹ቦታው የኔ ነው›› ብላ በማስረጃ አስደግፋ መሞገቷን እስካሁን ቀጥላለች። የሌሎች ዕምነት ድርጅቶች ተከታዮችም ሆኑ ግለሰቦች በበኩላቸው፣ “መሬት የመንግሥት ነው” በዚህም ማንኛውም ሕዝብ በቦታው መገልገል ይችላል ማለቱን ተያይዘውታል።

የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች በበኩላቸው፣ በመስቀል አደባባይ ሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ኹሉ፣ እኛም ጸሎት ማድረግና ለተፈናቃዮች ድጋፍ የማስባሰብ ሥራ በቦታው ላይ ማከናወን እንችላለን ሲሉ ተደምጠዋል።

ውዝግቡ እየተስተዋለ ያለው በተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥትና በኃይማኖት ተቋማቱም ጭምር ነው። ለአብነትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን የመስቀል አደባባይን ጉዳይ በሚመለከት ጥር 1/2014 ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ለማድረግ ያሰቡት ውይይት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ውይይቱ እንዳልተከናወነና በጉዳዩ ላይ ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ ቤተክርስትያኗ በመግለጫዋ አሳውቃለች።

በሌላ በኩል ከንቲባዋ የፊታችን ጥር 11/214 የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በማስመልከት ለጠቅላይ ቤተክህነት የእንወያይ ጥሪ ቢያደርጉም፣ የውይይት መድረኩን እንዳልተቀበለች ቤተ ክርስቲያኗ ባሳለፍነው ጥር ሦስት 2014 በሠጠችው መግለጫ መግለጿ ይታወሳል።
ታዲያ ይህ በእንዲህ ዓይነት ኹኔታ ከቀጠለ፣ በ2014 የሚከበረው የጥምቀት በዓል በተለመደው መልኩ እንዳይከበር ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋትም በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተነሳ ነው።

በመስቀል አደባባይ ጉዳይ ላይ የሚታየው አለመስማማትና ቅራኔ ሰሞኑን የተፈጠረ አይደለም። ችግሩ እልባት ሳይቸረው ዓመታትን ያስቆጠረ ጉዳይ መሆኑን ካሁን በፊት ያሉ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ለአብነትም በእስልምና ዕምነት ተከታዮች የሚከበረውን የረመዳን ወር የዒፍጣር ሥነ-ስርዓትን በአደባባዩ ለማካሄድ የተደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ በ2013 ግንቦት ወር ውስጥ ያልተጋባ ጭቅጭቅ ውስጥ ተገብቶ እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ መርሃ ግብሩን ግንቦት አንድ 2013 በመስቀል አደባባይ ላይ ለማክበር ቢታሰብም ውዝግብ በመነሳቱ፣ በዓሉ ከኹለት ቀን በኋላ ግንቦት ሦስት 2013 በዚሁ አደባባይ በመኪና መተላለፊያው መንገድ (አስፋልት) ላይ እንደተከበረ የሚታወስ ነው።

ይህ ጉዳይም በወቅቱ በእስልምና ኃይማኖት፣ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንና በመንግሥት በኩል ብዙ ክርክርና አለማስማማት አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል።

የመስቀል አደባባይ ጉዳይ ወደ ውይይት ቀርቦ ስምምነት ላይ ተደርሶ መፍትሔ ያልተገኘለት መሆኑ፣ ሰሞኑን ለተስተዋለው ተመሳሳይ አለመግባባት ዋነኛ ምክንያት ነው። እየተፈጠረ ያለው ውዝግብም፣ ችግር እየሆነና ከዓመት ወደ ዓመት የሚያስከትለው የሠላም መደፍረስ እየጨመረ ስለመሆኑ የሚስተዋሉ ነባራዊ ኹኔታዎች ምስክር ናቸው።

በ2013 በእስልምና ዕምነት ተከታዮች እና በቤተ-ክርስትያኒቱ መካከል የነበረው ጉዳይ ከቃላት ክርክር የዘለለ አልነበረም። ከሠሞኑን በመንግሥት፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንና በፕሮቴስታንት ዕምነት ተቋማት መካከል በተፈጠረው አለመስማማት የቤተ-ክርስትያን ጋዜጠኞች ታሥረው ተፈትተዋል፤ እንዲሁም በድንጋይ ውርወራና በአስለቃሽ ጭስ የተደገፈ ብጥብጥ ተስተውሏል።

በጥር 2014 የመጀመሪያ ሳምንት ለተስተዋለው አለመግባባት ሦስቱም ተቋማት የየራሳቸውን ምክንያት ሲዘረዝሩ ተስተውለዋል።

የፕሮቴስታንት ዕምነት ተቋም ለተከታዮቿ ያስተላለፈችው መልዕክት ‹‹ጥር አንድ 2014 ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በመስቀል አደባባይ በመገናኘት ታላቅ አምልኮና ምስጋና እናደርጋለን›› የሚል ነው።

የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮችን እንደሚሉት ከሆነ፣ በመስቀል አደባባይ የሚከናወነው ዝግጅት የመስቀል በዓል ብቻ ሳይሆን፣ የሙዚቃ ኮንሠርቶች፣ የመንግሥት መርሃ-ግብሮች እና በየወቅቱ የሚደረጉ የተለያዩ ተግባራትም ጭምር ናቸው።
ታዲያ የሚያነሱት ቅሬታ፣ እስከሁን ይህ ኹሉ ሲሆን ዝም ብላ የቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን፣ በአደባባዩ ላይ የእኛ ዝግጀት ሊከናወን ነው ሲባል ለምን ሞገተች ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ተከታዮች በበኩላቸው፣ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች በአደባባዩ ላይ ታላቅ አምልኮና ምስጋና እንደርጋለን ብለው ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ‹‹ቦታው የቤተክርስትያኗ መሆኑ እየታወቀ፣ ይህን መሰል ተግባር ለማድረግ ማሰብ የቤተክርስቲያኗን ርሥት እንወርሳለን እንደ ማለት ነው›› ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ አደባባዩ ላይ ‹‹የኔ ነው›› የሚባል ነገር እንደማይኖርና መስቀል አደባባይ የተገነባው በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለሆነ የሕዝብ እንደሆነ ሲናገሩ ነበር።
የቤተክርስትያኗ ተከታዮችም፣ ‹‹መንግሥት ያወጣውን ውጭ እንመልሳለን፤ ርስታችንን አንሰጥም›› የሚል ምላሽ ለመንግሥት እየሠጡ መሆኑ በተለያዩ የበይነ መረብ አውታሮችና ሚዲያዎች ሲደመጥ ተስተውሏል።

ታዲያ በብዙኅኑ በኩል እየተሠነዘረ ያለው ጥያቄና አስተያየት፣ ችግሩ ዕልባት የማይሰጥበት ምክንያት ምን እንደሆነ አለመታወቁና ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ አለመስማማቱ ሊጠነክር ስለሚችል ለችግሩ መፍተሔ መለገሱ ዛሬ ነገ የማይባል ተግባር መሆን እንዳለበት ነው።
መስቀል አደባባይ-ታሪካዊ ዳራ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን፣ መስቀል አደባባይ ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ከተባሉ ግለሰብ በስጦታ መልኩ እንደተበረከተላትና ካርታና ፕላን እንዳላት በምስል ጭምር ማስረጃዋን አስደግፋ ስታወሳ ተስተውላለች።
ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት ምሁራንም፣ መስቀል አደባባይ ከራስ ብሩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን እንደተሠጠ በበይነ መረብ ትስስራቸው እየመሰከሩ ይገኛሉ።

ለአብነትም ታሪኩ አበራ የተባሉ ግለሰብ፣ አደባባዩ ከራስ ብሩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ለመስቀል በዓል ማክበሪያ ተብሎ እንደተሠጣት በቴሌግራም ገጻቸው ጽፈዋል።

ታሪኩ እንደጻፉት ከሆነ፣ ራስ ብሩ ቀድሞ ሲኖሩበት የነበረው ቦታ የአሁኑ መስቀል አደባባይ እንደነበርና መጠሪያውም የራስ ብሩ ሜዳ ይባል እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ግለሰቡ “ከሜዳቸው ቀንሰው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን መስቀል ማክበሪያ ይሆን ዘንድ ቦታውን በርሥትነት የሠጡት (በገንዘብም ይሁን በነጻ) ወደውና ፈልገው ነው በማለት ጽፈዋል።

የታሪክና የሕግ መምህሩ አልማው ክፍሌ በበኩላቸው፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለመስቀል በዓል አከባባር ሲጠየቁ ስለቦታው ታሪካዊ አመጣጥ በሚከተለው መልኩ አስቀምጠው ነበር።

የመስቀል በዓል እስከ 1879 በእንጦጦ ማርያምና ራጉኤል ቤተክርስትያን፣ ከ1979 እስከ 1922 ደግሞ በአዲሱ ቤተ-መንግሥት ይካሄድ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሯ ምክንያት ከ1922 እስከ 1927 የበዓል ማክበር መርሃ ግብሩ ተቋርጦ ቆይቷል።
አጼ ኃይሌሥላሴ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከ1933 እስከ 1966 በእስጢፋኖስ ቤተ-ክርስትያን ሲከበር ቢቆይም፣ ደርግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ መስቀል የሚባል በዓል እንዳይከበር ተደርጎ ነበር። ከ1983 ወዲህ በብጹዕ አቡነ ጳውሎስና በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል በተደረገ ሥምምነት በአሁኑ መስቀል አደባባይ ላይ እንዲከበር ተወስኗል ሲሉ ታሪክን ማስረጃ አድርገው አብራርተው ነበር።

መፍትሔው ምንድን ነው?
አዲስ ማለዳ፣ በመስቀል አደባባይ ላይ በተለያዩ አካላት በየወቅቱ ለሚነሳው ክርክርና አለመግባባት መፍትሔው ምንድን ነው? አለመግባባቱና ጭቅጭቁ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ችግሩ እየተባባሰ ላለመምጣቱ ምን ዋስተና አለ? ስትል ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምሁራንን አነጋግራለች።

በወቅቱ ልንፈታው ያልቻልነውና የተጋረጠብን በቂ ችግር አለብን። እርሱ ሳያንሰን ሌላ ተጨማሪ ችግር መፍጠራችን በጣም የሚያሳዝን ቢሆንም፣ ኹሉም አካላት ተገናኝተው ቢወያዩበት መፍትሔ ይመጣል እንጂ ከዚህ የበለጠ ጭቅጭቅ አይፈጠርም የሚሉት፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌዴራል ፍርድ ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪው አንዱአለም በእውቀቱ ናቸው።

የሕግ አማካሪው ከሰጡት አስተያየት መገንዘብ የተቻለው፣ ጉዳዩ በውይይት መፈታት የሚችል ሆኖ ሳለ፣ እልህና ጉልበትን የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ መጠቀም ችግሩን የበለጠ ሊያወሳስበው የሚችል መሆኑን ነው።

የዕምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን በመስቀል አደባባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንና መንግሥትም መግባባት አልቻሉም። ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ የጥምቀትን በዓል ዝግጅት በተመለከተ ለቤተክርስትያኗ ያቀረቡት ጥሪ ተቀባይነት አላገኘም። ቤተክርስትያኗ ለዚህ ድርጊቷ የሠጠችው ምላሽም ነገር ከተበላሸ በኋላ እነርሱ ሲፈልጉን ብቻ ለምን ይጠሩናል የሚል ነው።

ታዲያ ይህ በመንግሥትና በቤተክርስትያኗ መካከል የተስተዋለውን አለመግባባት በተመለከተ “የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤ ይሄ የኔ አደባባይ ነው የሚባል ነገር የለም ብላ መወሰን የለባትም። ይልቁንም የኹሉንም የዕምነት ተቋማት ተወካዮች እየጠራች ብታወያይ ይሻላል። ካልሆነ ነገሩ የበለጠ ይባባሳል” በማለት የሕግ አማካሪው አንዱአለም በእውቀቱ ምላሽ ሰጥተውበታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን “አደባባዩ ከራስ ብሩ ነው የተሰጠኝ፤ የራሴ ካርታና ፕላን አለኝ ባይ ነች” ሌሎች የዕምነት ድርጅቶች ደግሞ “መሬት የመንግሥት ስለሆነ እኛም በቦታው አምልኳችንን ማንጸባረቅ እንችላለን” ባይ ናቸው።
በመሆኑም፣ አዲስ ማለዳ ባለይዞታ የሆነ አካል በይዞታው የመወሰን መብት አለው? መንግሥት ለግንባታ ወጭ ባደረገበት ቦታስ የባለይዞታው መብት ምንድን ነው? ስትል ለሕግ አማካሪው ጥያቄ አቅርባለች።

አንዱአለም በበኩላቸው፣ ከሕጉ አንጻር ባለይዞታ የሆነ አካል በይዞታው ላይ መወሠን ይችላል ብለዋል። ባለይዞታነቱ የሌላ አካል ሆኖ ሳለ ባለቤት ያልሆነው አካል ለቦታው ወጭ አውጥቶ ግንባታ ሲፈጽም ባለይዞታው ንብረቱን ሊያጣ ይችላል ወይ? የሚለውን ጥያቄም የሕግ አማካሪው በምሳሌ አስደግፈው ምላሽ ሰጥተውበታል።

መጀመሪያ ቤተ ክርስትያኗን ፈቃድ መች ጠየቋት የሚሉት አንዱአለም፣ “አንተ መጥተህ የእኔን ቤት ቀለም ብትቀባውና ከዛ በኋላ ቤት ውስጥ ለመግባት ብትፈልግ የአንተ ይሆናል ማለት አይደለም” ነው ያሉት። በተመሳሳይ ለዚህ አደባባይ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ካርታና ፕላን እያላት ሌላ አካል ገንዘብ ስላወጣ የእርሱ ሊያደርገው የሚችልበት መንገድ እንደሌለ ነው ያስረዱት።

ከዓመታት በፊት መንግሥት የመስቀል አደባባይን ግንባታ ሲያከናውን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅሬታ አቅርባ መንግሥት ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።
ታዲያ መንግሥት ለአደባባዩ ወጪ ከማድረጉ ጋር በተያያዘ ከሕግ ባለሙያዎች የተገኘው ምላሽ፣ መንግሥት ግንባታውን ከማከናወኑ በፊት የቦታውን ባለቤት ፈቃድ መጠየቅ ነበረበት የሚል ነው።

“አዳነች አበቤ መስቀል አደባባዩ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተሠራ ስለሆነ የሕዝብ ነው” ማለታቸው ኹሉን ቅር አሰኝቷል የሚሉት የሕግ አማካሪው፣ መንግሥት ግንባታ ከማድረጉ በፊት ቤተ ክርስትያኗን ፈቃድ አልጠየቃትም፤ ስለዚህ ፈቃድ ሳይጠይቅ ግንባታውን ገንብቶ የሕዝብ ነው ማለት እንደማይቻል ነው ከሕጉ አንጻር ማብራሪያ የሰጡት።

እንደ ሕግ አማካሪው ገለጻ ከሆነ፣ መንግሥት የሚያነሳው መከራከሪያ ተቀባይነት ሊኖረው ይችል የነበረው ግንባታውን ከማከናወኑ ቀድሞ ባለይዞታውን ፈቃድ ጠይቆ ባለይዞታው አቅም የለኝም መገንባት ትችላለህ የሚል ምላሽ ቢሰጥ ኑሮ እንደነበር ነው።
ጉዳዩ ከሕግ አንጻር ሲታይ፣ ፈቃድ ካልተጠየቀና ካልተገኘ አንድ ንብረትነቱ የሌላ አካል የሆነን ቦታ “ገንዘብ ስላወጣህ ብቻ ያንተ አያደርገውም” የሚሉት አንዱአለም፣ ቤተ ክርስትያን ክርክሯን አቅርባ መንግሥትም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ጉዳዩን መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል ባይ ናቸው።

ከዚህ በፊት ቤተ ክርስትያኗ በተመሳሳይ ጉዳይ በደል ደርሶብኛል ብላ ጥያቄዋን ወደ ሕግ አቅርባ መፍትሔ ሲሰጣት እንደሚያውቁ የጠቆሙት የሕግ አማካሪው ፣ ደርግ ወስዶባት የነበረውን አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ አካባቢ የሚገኝ መሬቷን በሕግ አስመልሳለች ሲሉ አስታውሰዋል።
አያይዘውም፣ በቤተ ክርስትያን፣ በመንግሥትና በሌሎች የዕምነት ተቋማት በኩል የሚስተዋለው ውዝግብ ወደ ሕግ ቀርቦና ክርክር ተደርጎበት ውሳኔ ሊሰጥበት የሚችል ቀላል ጉዳይ ነው ሲሉ መክረዋል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ ተከታዮች ግር ብለው በመሔድ ሳይሆን፣ በተወካዮቻቸው አማካይነት ጥያቄያቸውን ማቅረብ አለባቸው ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

የመንግሥትም ሆነ የኃይማኖት ተቋማት፣ በሰዎች መካካል አለመግባባት ሲፈጠር ከተቻለ ተበደልኩ ባይና በደል አድርሷል የሚሉት አካላት በጠረንጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ችግራቸውን እንዲፈቱ፣ ካልሆነ ደግሞ ሕግንና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ ማንኛውንም ችግር ሥር ሳይሰድ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መፈታት እንዳለበት ጥንቅቅ አድርገው ያውቃሉ።

በመሆኑም፣ የመስቀል አደባባዩ ጉዳይ የንብረት ጥያቄ ስለሆነ፣ ማንኛውም አካል በሕጉ መሠረት ጥያቄውን አቅርቦ ውሳኔ ላይ መድረስ ተመራጭ መሆኑን ነው ለጉዳዩ ቅርብ ከሆት የሕግ አማካሪው የተሠነዘረው የመፍትሔ ሐሳብ።

የመስቀል አደባባይ ውዝግብ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የ2014ን የመስቀል በዓል በሠላም ለማክበር ኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here