በመስቀል አደባባይ ላይ የተነሳ አምባጓሮ

0
787

ሠሞኑን ከመነጋገሪያነት አልፈው በቃላት መሸነቋቆጫ ከሆኑ ጉዳዮች ቀዳሚው በመስቀል አደባባይ ላይ የተነሳው አምባጓሮ ነው። በቀደመው መንግሥት አብዮት አደባባይ ሲባል የኖረውና በኢሕአዴግ ዘመን ወደ ሕጋዊ ባለቤቱና ስሙ እንደተመለሰ የሚነገርለት አደባባይ፣ ኃይማኖትና ዘር ሳይለይ የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን መገልገያ ሆኖ ቆይቷል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ይዞታዎች የነበሩ መሬቶች ለኮንዶሚኒየምም ሆነ ለሌላ ዓላማ እየተባሉ፣ አንዳንዴም ለገበያ እንዲውሉ በመንግሥት መወረሳቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ሲሠማ ነበር። በተለይ ሆሳዕናን በመሳሰሉ የክፍለ አገራት ከተሞች የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ተወሰደብን በሚል ለዓመታት በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ጠፍቶ ምዕመኑ በደል እንደደረሰበት ሲናገር ቆይቷል።

በይዞታ ይገባኛል መንግሥትና የኃይማኖት መሪዎች ውዝግብ ውስጥ እየገቡ ቆይተው የጃንሜዳው ጉዳይ ጎልቶ ወጥቶ ነበር። ከዛም አስቀድሞ የመስቀል አደባባይ ዕድሳት ጋር በተገናኘ ቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድ አለመጠየቋን በማንሳት በመቃወሟ መንግሥት ይቅርታ ጠይቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ርክክብ እንደሚደረግላት ቃል ተገብቶላታል ተብሎ ውጥረቱ ረግቦ ነበር። ኹኔታው ተድበስብሶ ማረጋገጫ የጠየቀችው እያለች፣ ይዞታ ላልነበራቸው ለኢሬቻ ዕምነት ተከታዮች በቅድሚያ ቦታ ከነማረጋገጫው ተሰጣቸው ብለው አነጻጽረው ሒደቱን የታዘቡ ነበሩ።

የአደባባዩ ዕድሳት እንዳለቀ የአፍጥር ሥነ-ስርዓት ሊካሄድበት ነው በመባሉ የሠሞኑን ዓይነት ተቃውሞ አስነስቶ ቀኑ እንዲተላለፍና የመንግሥት ይዞታ በሆነው በአውራ ጎዳናው ላይ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር። በዚህም ወቅት ጉዳዩ እልባት ስላልተሰጠው ለሰሞኑ አምባጓሮ ምክንያት ሁኗል።

የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች በአደባባዩ የጸሎት መርሃ ግብር ለማካሄድ ማስታወቂያ ማስነገር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በይዞታችን ላይ ዕውቅና ያልሰጠነው ፕሮግራም እንዳይካሄድ ብለው ለመንግሥት አቤት እንዳሉ ቢናገሩም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለው ወቅቱ መድረሱን ተናግረዋል። ቀኑ ሲቃረብ ደግሞ አንድ የፕሮቴስታንት ዕምነት መሪ ተናገሩ የተባለ የዕንውረስ ጥሪ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመኑ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ በተወሰኑ የዕምነቱ መሪዎች ዘንድ ትችት ተሰንዝሮበት ነበር።

በኹለቱም ወገን ነገሩ እየተካረረ ሲመጣ መንግሥት ዝም ማለቱ ያስገረማቸው አንዳንዶች፣ የኹለቱ ዕምነት ተከታዮች እንዲባሉ የሚፈልግ ወገን እንዳለ በግልጽ የታየበት ነው እያሉ ሒደቱን ገምግመውታል። በዚህ መልክ ቀኑ ደርሶ የተፈራው ሁኖ ብጥብጥና አምባጓሮ በመጠኑም ቢሆን ተከስቶ ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው። ይህም ሲሆን ማስታረቅ የሚገባው መንግሥት በሹሙ አማካይነት አንዱን ደግፎ በሕግ የተሠጠን የባለይዞታነት መብት ሽሮ፣ ቦታው የኹሉም ነው፤ በነዋሪው ግብር የተሠራ ነው፤ ማለቱ ጉዳዩን የበለጠ አካረረው።

መንግሥት ራሱ በሕገ-ወጥ መንገድ የመንግሥት ይዞታ ላይ ቤት ተሠርቷል እያለ በሚያፈርስበት ዘመን፣ ስለሠራሁበት እወርሰዋለሁ ማለቱ ብዙዎችን አሳዝኗል። አንዳንዶች ደግሞ ገንዘቡን እንመልሳለን ቢሉም የተወሰኑት በመንግሥት ወጪ የታደሱ የእማማ ዝናሽ ዓይነት ቤቶች የመንግሥትና የሕዝብ ይሆናሉ ማለት አይደለም በማለት ሐሳቡን ኮንነዋል። ግንባታው ሲጀመር ይቅርታ ተጠይቀው እንዲጎበኙ የተደረጉት የባለይዞታዋ አባቶች እንጂ፣ የሕዝብ ተወካዮች አይደሉም በማለት የአንዱን ነጥቆ የኹሉም እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፣ በሠላም አብሮ ለመኖር ለኹሉም እንደየአቅማቸው የራሳቸው እንዲኖራቸው ማድረጉ ይሻላል ያሉም አሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here