‹‹የፓርቲ አባል በመሆናቸው የታሰሩ ዜጎች የሉም›› የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት

Views: 198

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፓርቲ አባል በመሆኑ በጸጥታ ኃይሎች የታሰረ ዜጋ የለም ሲል ከዚህ ቀደም የቀረበበት ወቀሳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታወቀ።
ባለፉት ኹለት ሳምንታት ወስጥ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላቶቻችን ታስረውብናል ቢሉም፣ የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የፓርቲ አባል ስለሆነ ብቻ የታሰረ ሰው የለም ሲል ለአዲስ ማለዳ ምላሹን ሰጥቷል።

ቢሮው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላቶች መታሰራቸውን ቢያስተባብልም፣ ከሳምንት በፊት የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ ጽሕፈት ቤት፣ አርማና ባነሮቼ ተቃጥለውብኛል፣ ወለጋ ዞን ቢንቢ ከተማ ላይ ጽሕፈት ቤታችን ተዘርፎ የመንግሥት የወታደር ካምፕ ሆኗል ሲል ምሬቱን ገልፆ ነበር።

የኦፌኮ ቢሮ ኃላፊ ጥሩነህ ገመታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ፓርቲያቸዉ እስከ የካቲት 11/ 2012 ድረስ 27 አባላቶቹ ታስረውበታል። ከእነዚህም ውስጥ ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ የሆናቸዉ በምዕራብ ወለጋ ዞን የፓርቲዉ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም ዲአና፣ ለሦስተኛ ጊዜ የታሰሩና የምእራብ ጉጂ ዞን የኦፌኮ ዋና ጸሐፊና የማእከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጃተኒ ምትኩ ይገኙበታል። በተጨማሪ በአምቦ አካባቢ 25 አባሎቻቸዉ ያለአግባብ እስር ላይ መሆናቸዉን ጥሩነህ ተናግረዋል።

ጥሩነህ እንደሚሉት፣ አባሎቻቸዉ የታሰሩት ያለ በቂ ምክንያት ነው። አንዳንዶቹ ለምን እንደታሰሩ እንኳን እንዳልተገለፀላቸውና፣ በማያውቁት ምክንያት በእስር ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊዉ ገለፃ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት እንደሆነና የገዥዉ ፓርቲ ያለአግባብ የሚያደርገው ድርጊት ነው ሲሉ ተናግረዋል። አክለዉም ይህ የሚሳየዉ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደገና እየጠበበ መምጣቱን ነዉ ብለዋል።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ባሳለፍነዉ ኹለት ሳምንታት ብቻ ከ400 በላይ አባላቶቹ እንደታሰሩበት የፓርቲዉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሚካኤል ቦረን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አባሎቹ የታሰሩት በባሌ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በአምቦ፣ በቡራዩና በመቱ እንደሆነ ሚካኤል አክለዉ ገልፀዋል።

በክልሉ የጅምላ እስር አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ያሉት የኦነግ ሥራ አስፈፃሚ፣ እስሩ በምርጫ ዋዜማ መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገዉ ገልፀዋል። የእስር ሂደቱ እየጨመረ የመጣበት ምክንያት፣ በምርጫ ዋዜማ የፖለቲካ ጫና ለማድረግ የታሰበ ነዉ ሲሉም ተናግረዋል።

በተቃራኒው የኦሮሚያ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ፣ በክልሉ የኦፌኮም ሆነ የኦነግ የፓርቲ አባል ስለሆነ የታሰረ ሰው እንደሌለና የፓርቲ አባል ስለሆነ የታሰረ ሰው ስለመኖሩ ክልሉ መረጃ እንደሌለዉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ንግግር፣ የታሰሩ ሰዎች ካሉም በሠሩት ወንጀል እንጂ የፓርቲ አባል ስለሆኑ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኮማንደር ጉደሳ ጉተማ፣ የኦነግና ኦፌኮ ቅሬታን እንዳሰሙ በመግለጽ፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ብትጠይቅም ኮማንደሩ ጥያቄዉን ካዳመጡ በኋላ ከአዲስ ማለዳ ጋር የነበራቸዉን የስልክ ግንኙነት ተቋርጧል፤ ስልካቸውንም አጥፍተዋል። ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።

የኦሮሚያ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ ማክሰኞ የካቲት 10/2012፣ የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት መደበኛ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ራሳቸውን ነጻ አውጪዎች ነን ብለው የሰየሙ ሽፍቶች በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት መዋቅር ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን መግለጻቸው ይታወሳል። መንግሥት ሕግን የሚጻረሩ እንስቃሴዎችን ሁሉ እያጤነ የሕግ የበላይትን ለማስፈን ቁርጥ አቋም ይዞ እየሠራ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com