የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ17 ሺሕ ሠራተኞቹ የብድር አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Views: 513

ከአፍሪካ በትርፋማነቱ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ17 ሺሕ በላይ ሠራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር አገልግሎች መጀመሩን አዲስ ማለዳ አረጋገጠች። ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በገጠማቸው ወቅት ተግባራዊ የተደረገው አገልግሎቱ፣ ከታችኛው የሥራ መደብ እስከ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን ለመስጠት ያሰበው በቋሚነት በተቋሙ ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞቹ ሲሆን፣ ለመኪና መግዣ እና ለቤት መግዣ የሚሆን የብድር አገልግሎት ከተሰጠ በኋላ ከደሞዛቸው ላይ ተቆራጭ እንደሚሆን ታውቋል።

የብድር አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉን ያማከለ ባለመሆኑ ምክንያት በሠራተኞች በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም የአየር መንገዱ አብራሪዎች የፈለጉትን የብድር መጠን እንዲወስዱ የሚፈቀድ የነበረ ሲሆን፣ የበረራ አስተናጋጆች ደግም አጠቃላይ ገቢያቸው ከ50 ሺሕ ብር ካልሆነ አገልግሎቱን የማግኘት መብት አልነበራቸውም። የበረራ አስተናጋጆቹ ይህንን እንኳን ቢያሟሉ ከ 300 ሺሕ ብር በላይ የመበደር እድሉ እንዳልነበራቸው ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በዚህም የተነሳ አሰራሩ ከተለያዩ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ዘንድ ቅሬታ በማስነሳቱ ምክንያት ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ አዲሱ የብድር አገልግሎት ስርአት እንደተጀመረ አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የድርጅቱ የሥራ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲሱ የብድር አገልግሎት የአየር መንገዱ ሠራተኞች ከሚበደሩት የገንዘብ መጠን አምስት በመቶ እንዲቆጥቡ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ብድሩም 9 ነጥብ 75 በመቶ ወለድ እንደሚኖረውም ተገልጿል። የብድሩንም አገልግሎት ለመስጠት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአየር መንገዱ ጋር ስምምነት መፈፀሙን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር የሺዋስ ፋንታሁን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ብድር አገልግሎቱ መጀመሩን እንደሚደግፉ ተናግረው፣ ነገር ግን ቀጣይነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የብድር አገልግሎቱን ለማስጀመር እንቅስቃሴ ከተጀመረ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ያለፈው ሲሆን፣ አሁንም አየር መንገዱ እንደሚለው ሁሉንም ሠራተኞች ተጠቃሚ ያደርጋል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

አሁንም እንደ አዲስ ተግባራዊ የተደረገው የብድር አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ብዙም ልዩነት የለውም ያሉት የሺዋስ፣ ከአውሮፕላን አብራሪዎች እና ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙት ውጪ ሌሎችን ቢያካትትም ተጠቃሚ አያደርጋቸውም ብለዋል።

በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የቤት መሥሪያ ብድር ተጠቃሚ የነበሩትንም አዲሱን የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሱት የሺዋስ፣ አሰራሩ ጥቂቶች ሀብት እንዲያካብቱ፤ ሌሎች ተጠቃሚ ያልነበሩት ደግሞ ለሟሟያ ብቻ መግባታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ አገልግሎቱን ለመጀመር አስቦ እንደ አዋሽ፣ ሕብረት፣ ዳሽን እና ዘመን ባንኮች ጋር በተለያዩ ጊዜ ስምምነት ላይ ተደርሶ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተቋርጦ ነበር።

ከዚያም አየር መንገዱ ከሕብረት ባንክ ጋር ስምምነት ተደርጎ፣ የብድር ስርአቱ ተግባራዊ ለመሆን የአየር መንገዱ ሠራተኞች የደሞዝ አከፋፈል ሂደት በባንኩ እንዲያልፍ እና ወለዱም ዘጠኝ ነጥብ አንድ እንደሚሆን ተስማምተው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ከ800 በላይ የሚሆኑ የአየር መንገዱ ሠራተኞች የባንክ አካውንት ከከፈቱ በኋላ አየር መንገዱ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሐሳቡን መቀየሩን የሺዋስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን እንዲሰጧት የአየር መንገዱን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሄኖክ ሲራክን ብታነጋግርም፣ መረጃ አልሰጥም በማለታቸው ጥረቷ አልተሳካም።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com