ኢትዮጵያ ከ‹ካርበን› ሽያጪ ከ490 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘች

ኢትዮጵያ ከካርበን ሽያጪ ከ 490 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት አስታወቀ።

በ2013 እና በተያዘው ዓመት በምዕራብ አርሲ፣ ምሥራቅ ባሌና ባሌ ዞን በሚገኙ ደኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ምንጣሮ መቀነስ እንደተቻለ እና ፈረንሳይ አገር ለሚገኘው ‹ኪኮ አርክ› ለተሠኘ ድርጅት 9.9 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ እንደተሸጠ ተመላክቷል። በዚህም 490 ሚሊዮን 744ሺሕ 744 ብር ገቢ ማስገኘት እንደተቻለ የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ዋና ኃላፊ አራርሳ ለጋሳ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በድርጅቱ በኩል ቅድሚያ ምንም ዓይነት ዕቅድ ያልተያዘ ቢሆንም፣ ሽያጩ በኹለት ዙር እንደተካሄደ ተገልጿል። በመጀመሪያ ዙር 5.5 ሚሊዮን ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ በመሸጥ 149 ሚሊዮን 256 ሺሕ፣ 566 ብር የተገኘ ሲሆን፣ በኹለተኛው ዙር 4.4 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ለሽያጭ ቀርቦ 340 ሚሊዮን 488 ሺሕ 154 ብር ተገኝቷል ተብሏል። በአጠቃላይ ከተሸጠው ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ከአምስት ሚሊዮን ዮሮ በላይ ገቢ በማግኘት በድምሩ ከላይ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ለኢትዮጽያ ማስገባት መቻሉን አራርሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ከተገኘው ገቢ 60 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የደኑን ምንጣሮ ለመከላከል በሕጋዊ መንገድ ለተቋቋሙ 64 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሰጠ ሲሆን፣ ቀሪው 40 በመቶ ለድርጅቱ ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

እነዚህ ማኅበራት ከድርጅቱ ጋር ውል ተፈራርመው ወደ ሥራ የገቡ እና በደኖቹ አከባቢ የሚገኙ የማኅበረሠብ ክፍሎችን ተሳታፊ ያደረጉ ሲሆን፣ ከካርበን ሽያጩ ከሚገኝ ገቢ በተጨማሪ፣ የደን ምንጣሮን የመከላከል እና ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት አደን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እንደሚሠሩ ተገልጿል።

ከካርበን ሽያጩ የተገኘውን ገቢ እንደተሠማሩበትና እንደተቀበሉት የደን ሥፋት መጠን ማኅበራቱ እንደተከፋፈሉት ኃላፊው ተናግረዋል።

ድርጅቱ በሕጋዊ መንገድ ለተደራጁ ማኅበራት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን፣ ተጨማሪ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሠማርተው እንዲሠሩ ኹኔታዎችን ያመቻቻል ተብላል።

የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት፣ በክልሉ ያለውን የደን ምንጣሮ በመከላከል እና ተጨማሪ ደን በማልማት ከካርበን ዳይ ኦክሳይድ ገቢ እንዲገኝ ከ ሦስት ዓመት በፊት ዕቅድ ይዞ ወደ ሥራ ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በበጀት ዕጥረት እና የካርበን ገዥ ድርጅቶችን ማግኘት አለመቻሉ ዕቅዱ ላይ ዕንቅፋት እንደፈጠረበት ተገልፃል።

በቀጣይ ከካርበን ሽያጪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ደኖች ላይ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በጋራ እንደሚሠራ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በክልሉ ያለውን የደን ሽፋን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉ የዱር እንስሳት እንዳይሰደዱ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ኃላፊው አክለውም፣ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ደን የማልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ለፓርኮችም ትኩረት በመስጠት ብርቅዬ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here