ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር

0
1271

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ወቅት በክልሎችም ሆነ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ከተማ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ  ሲዘዋወር ተያዘ የሚል መረጃ በተደጋጋሚ ይሰማል።

ይህ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ይልቁንም የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲያነሱ ይደመጣሉ።

ካለፉት ኹለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር በሰፊው ከሚከናወንባቸው አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ መሰለፏን የፌዴራል መንግሥት ጭምር ሲገልጽ ቆይቷል።

የጦር መሣሪያዎች በቀላሉ መገኘት፣ የኅብረተሰቡ ጦር መሣሪያ የመታጠቅ ፍላጎት መጨመር እና ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ባሏት ድንበሮች ላይ ያለው ቁጥጥር ማነስና ተያያዥ ምክንያቶችም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በስፋት እንዲስፋፋ እንዳደረጉም በተለያየ ጊዜ ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለፖለቲካ ዓላማም እየዋለ መሆኑን መግለፁ አይዘነጋም። ለአብነትም የአገሪቱን መረጋጋት የማይፈልጉ ያላቸው ኃይሎች ዝውውሩ ውስጥ እንዳሉበት አስታውቋል።

በአገሪቱ ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በርካታ ወንጀሎች እየተሠሩ ስለመሆናቸውንም መንግሥት ሲገልፅ እንደነበር እና በጦር መሣሪያ ዝውውሩ የሚፈፀሙ ወንጀሎች አሁንም እንዳልቆሙ እየተወሳ ነው።

ኢትዮጵያ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣ በኬንያ በምትዋሰንባቸው ድንበሮች በኩል የጦር መሣሪያዎች በብዛት እየገቡ መሆኑ እና ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖር አድርጓል ሲል ያወሳው የፌዴራል ፖሊስ ነው።

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ በጉልህ ከታየባቸው ክልሎች የጋምቤላ ክልል፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እና የአማራ ክልል በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው።

በጋምቤላ ክልል የውስጥና የድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ከአንድ ሳምንት በፊት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ተናግረው ነበር።

የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በጋምቤላ ከተማ ባካሄደበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፣ በክልሉ የውስጥና ድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ውስጥ በመግባት በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ከሚፈጸሙት ጥቃት በተጨማሪ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቀንድ ከብቶች በተደጋጋሚ ዘርፈው ሲወስዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

የጥፋት ኃይሎች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመከላከል መንግሥት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም በስብሰባው ወቅት አስረድተዋል።

‹‹ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር /ጋነግ/ ብሎ የሚጠራው የአሸባሪ ቡድኖቹን የሕወሓትና ሸኔ ተላላኪ እኩይ ሴራውን ለማምከን በክልሉ መንግሥት በኩል በትኩረት እየተሠራ ነው›› ሲሉ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ጨምሮ በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት የሚፈጽመውን ወንጀሎች በመከላከል ረገድ ከጸጥታ አካላቱ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም  ተጠይቋል።

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡቶው ኡኮት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በክልሉ በየወቅቱ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዳለ እና ይህንንም ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

አክለውም፣ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ድንበር ዘለል ዘርፊያዎችንና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ሊፈጥሩ የሚችሉትን የጸጥታ ችግር ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር ብዛት ያላቸው የልዩ ኃይል የፖሊስ አባላትን በማሠልጠን ወደ ስምሪት እንዲገቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው የሚገኙ የሚሊሻ አባላትን አቅም በሥልጠናና በግብዓት የማጠናከር ሥራም እየተካሄደ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና ሌሎችን የወንጀል ችግሮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ አካላትን ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግም አስረድተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መለስ በየነ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት ወራት በክልሉ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሲዘዋወር የሚያዝበት እድል እንደነበር እና አሁን ላይ የቁጥጥር ስርአቱን ማጠናከር በመቻሉ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል።

ለቀጣይም በክልል ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ የሰላምና ፀጥታ ኮሚቴ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኃላፊው በተጨማሪም ኮሚቴው በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ባሻገር ክልሉ በሚያዋስናቸው አካባቢዎች መውጫ እና መግቢያ ድንበሮች ላይ የፀጥታ አካላትን በማጠናከር የፍተሻ እና የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በመዲናዋ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዳይስፋፋ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረግኩ ነው ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ በየወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች እየተገኙ መሆኑን እና ይህን ሕገ ወጥ ተግባር ለመቆጣጠርም ኮሚሽኑ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ እንደተናገሩት፣ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በመዲናዋ በእንቅስቃሴ ላይ ቢሆኑም፣ በዚያው ልክ ቁጥጥሩም ጠንካራ እንደሆነ እና በቀጣይም ኮሚሽኑ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ የፌዴራል መንግሥት ቀደም ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው 1177/2011 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ማንኛውም የጦር መሣሪያ ሊያዝ የሚችለው በሚሊሻ ጽሕፈት ቤት፣ በፖሊስ ጽሕፈት ቤት አልያም በሰላም ጽሕፈት ቤት አንድ ግለሰብ አመልክቶ፣ ሕጋዊ ፍቃድ ሲሰጠው ነው። ከዛም አንድ የጦር መሣሪያ ብቻ የሚይዝበት እድል አለ ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ፍቃድ ሳይኖረው ማንኛውም አካል ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ማዘዋወር፣ የጦር መሣሪያ መነገድ፣ የጦር መሣሪያ መደበቅ ወይም ፍቃድ ሳይኖረው ይዞ መገኘት እና መንቀሳቀስ የእስራት ቅጣት እንደሚያስቀጣ እና የወንጀሉ ክብደት እና አፈፃፀም ታይቶ ከሦስት እስከ ዐስር ዓመት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ድርጊት መሆኑን የሕግ ባለሙያው  ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች እና በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው የሚስተዋለው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እየተስፋፋ መሆኑን ያነሱት የሕግ ባለሙያው፤ በመንግሥት በኩል ቸልተኝነት እና የቁጥጥር ክፍተት እንዳለ ማሳያ ነው ይላሉ።

ከዚሁ ጋር አያይዘውም አንዳንድ አካላት የጦር መሣሪያን በስፋት ከማንቀሳቀስ ባሻገር ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአገር ከመከላከያ ሠራዊት ውጭ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት የሰው ሕይወት እንዲሁም ንብረት የሚወድምበት ሁኔታ እየሰፋ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግሥት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ሲስፋፋ እያየ የጦር መሣሪያ አዋጅ ከማውጣት ባለፈ ጉዳዩን በቸልተኝነት ወይም በትኩረት እየተከታተለ አለመሆኑን ያሳያል ባይ ናቸው።

የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ መንግሥት በቀጣይ ከሕጋዊ ፍቃድ ውጭ ከአንድ በላይ የጦር መሣሪያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን በአግባቡ በሕግ ቁጥጥር ስር አውሎ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በትኩረት መሥራት የተሻለ ነው ብለዋል።

ይህን ማድረግ ካልተቻለ የእርስ በእርስ አላስፈላጊ ግጭትን እንደሚያጠናክር እና ለሌሎች ተጨማሪ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አሳስበዋል።

መንግሥት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የመቆጣጠር አቅም እና ዝግጅቱ አለኝ የሚል ከሆነ በተግባር ውጤታማነቱን ከማሳየት ባሻገር የጦር መሣሪያ ዝውውርን መቆጣጠር የሚያስችለውን ልምድ ካላቸው አገራት እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችን በማማከር በትኩረት እንዲሠራ የሕግ ባለሙያው አመልክተዋል።

ከውጭ አገራት የሚገቡ ሽጉጥ፣ ክላሽ እና ሌሎች ተያያዥ የጦር መሣሪያዎች ድንበር ላይ በሚገቡበት ወቅት የፍተሻ እና የቁጥጥር ሥራውን ከማጥበቅ በተጨማሪ በኮንትሮባንድ ወይም በሕገ መጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የመሣሪያ ምንጮችን ማድረቅ ከተቻለ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩን መቆጣጠር የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን እና ኅብረተሰቡም ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ነፃ የሚሆንበት እድል ሰፊ መሆኑን  ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here