ሰባት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረጋቸው ተገለፀ

ሰባት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረጋቸውን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ የተለያዩ የግዥ ስርዓትን ለማዘመን በአሁን ወቅት የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ለትግበራ ከተመረጡ ተቋማት ዘጠኙ የተቋማቸውን አደረጃጀት እና ዕቅድ ወደ ስርዓቱ ማስገባት ችለዋል ብለዋል። ከነዛም መካከል ሰባት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ አድርገው መጠቀም እንደቻሉ እና ኹለቱ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም ስርዓቱ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከባንኮች ጋር የተናበበ እንዲሆን፤ መደበኛ የጨረታ ሠነዶችን በሲስተሙ ላይ የማዋቀር ተግባር እንደተጠናቀቀ ባንኮች ሲስተሙን ተጠቅመው ለተጫራቾች የጨረታ ማስከበሪዎችን እንዲያስይዙ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን ለመተግበር እንዲችሉ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲያደርጉ በተሠራ ክትትል እና ድጋፍ፤ በበጀት ዓመቱ ለትግበራ ከተመረጡ መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ የሌሎች 57 መሥሪያ ቤቶችን የግዥ ዕቅዶቻቸውን በዚሁ ስርዓት ይፋ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ኃላፊው አያይዘው እስከ አሁን ባለው 232 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ግዥ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሥራ እቅዳቸውን በኦንላይን በስርዓቱ መሠረት እያስገቡ እንደሚገኙ እና በሂደት ሙሉ ለሙሉ የግዥ ስርዓቱን ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ከላይ ለተጠቀሱት የግዥ ስርዓቱን ለሚጠቀሙ የመንግሥት ተቋማት የተለያዩ ሽያጭ የሚፈፅሙ የንግድ ድርጅቶም ለምዝገባ የሚያገለግላቸውን የሲስተሙ አካል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደታሰበ እና እስከ አሁን ባለው 1134 አቅራቢዎች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው መመዝገባቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

ይህ የኤሌክትሮኒክስስ ግዥ ስርዓት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በመንግሥት በጀት የሚከናወኑ ማናቸውንም የመንግሥት ተቋማት ግዥ ማለትም ዕቃ፣ አገልግሎት፣ የግንባታ ዘርፍ ሥራ እና የምክር አገልግሎት ግዥ በይነ መረብን  በመጠቀም ከግዥ እቅድ እስከ ውል አስተዳደር ያሉትን ተግባራት ማከናወን የሚያስችል ሥርዓት መሆኑ ተጠቁሟል።

ስርዓቱ የግዥ ዕቅዶችን፣ መግለጫዎችን፣ የጨረታ ማስታወቂያዎችን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተጨማሪ የግዥ ተጫራቾችን መጋበዝ፣ የጨረታ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የሃራጅ ጨረታ ሂደቶችን ማካሄድ፣ የጨረታ ግምገማዎችን ማካሄድ፣ የጨረታ አሸናፊዎችን ማሳወቅ፣ የውል አስተዳደር ሥራዎችን ማከናወን፣ መረጃ እንደ አስፈላጊነቱ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እና መረጃዎችን መተንተን፣ የአቅራቢዎችን ዝርዝር መመዝግብ፣ የጨረታ ሰነዶችን በሽያጭም ሆነ በነጻ እንዲገኙ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቅሷል።

የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓቱ ተግባራዊ መሆኑ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ የግዥ ስርዓቱ ግልጽነትን የተላበሰ እንዲሆን እንደሚያስችል እና ከደንበኞች ጋር ያለውን ቀጥታ ግንኙነት ከመቀነስ ባሻገር ሙስናን መቀነስ እንደሚያስችል ተገልጿል።

በተጨማሪ ተጠያቂነትን ያሰፍናል፣ ሰፊ ተደራሽነትን ይፈጥራል፣ አስተዳደራዊ ወጭዎችን መቀነስ ያስችላል፣ ለግዥ አፈጻጸም የሚፈጀውን ጊዜ ያሳጥራል፣ ውድድርን ያስፋፋል፣ ፍትሃዊነትንም ያጎለብታል ተብሏል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በጥናት ላይ ተመርኩዞ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የፌዴራል መንግሥት በጀት ለግዥ የሚውል ነው ብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here