በዘጠኝ ወራት ከቆዳና የቆዳ ምርቶች 52.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

0
1416

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቆዳና የቆዳ ምርቶች 52.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ከሐምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2014 ባሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 61 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ማግኘት የተቻለው 52.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ ብሩክ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቡድን መሪው አክለውም በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ከ61 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ ከላይ የተጠቀሰው ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ጦርነት ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጽያ ላይ የጣለውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ መስመር ወይም የአጎዋ ማአቀብ ተከትሎ የጫማ እና አንዳንድ የቆዳ ምርቶችን በሚጠበቀው ልክ ወደ አሜሪካ መላክ ባለመቻሉ ለታቀደው እቅድ አለመሳካት በምክንያትነት ተጠቃሽ መሆኑን የቡድን መሪው ብሩክ ጠቅሰዋል።

በ2014 ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ በመላክ ለማግኘት የታቀዱ እቅዶችን ሲዳሰሱ፣ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች 51 ሺሕ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 27 ሺሕ 291 ዶላር ማግኘት ተችሏል ተብሏል። በከፊል ከተጠናቀቀ እና ሙሉ ለሙሉ ካለቀ የቆዳ ምርቶች ደግሞ 33 ሺሕ 977 ለማግኘት ቢታቀድም፣ 18 ሺሕ 411 ዶላር ተገኝቷል።

በተጨማሪ ከጫማ ምርቶች 9 ሺሕ 104 ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፣ 2 ሺሕ 738 ዶላር እንዲሁም ከጓንት 3 ሺሕ ዶላር ለማግኘት ሲታቀድ፣ 2 ሺሕ 280 ዶላር ማግኘት መቻሉን ቡድን መሪው ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች 26 ሺሕ 164 ዶላር፣ በከፊል ከተጠናቀቀ እና ሙሉ ለሙሉ ካለቁ የቆዳ ምርቶች 16 ሺሕ 719 ዶላር ተገኝቷል። በተጨማሪ ከጫማ ምርቶች 3 ሺሕ 449 ዶላር እንዲሁም ከጓንት 2 ሺሕ 398 ዶላር መገኘቱ ይታወቃል።

ምንም እንኳ በዘጠኝ ወራት ይገኛል ከተባለው ገቢ አንጻር ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ10 ሺሕ ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችል ሥልጠና መስጠት በመቻሉ፤ ከባንኮች፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከተለያዩ ባለ ድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት የተጠናከረ ሥራ መሥራት መቻሉ ለለውጡ መመዝገብ እንደሚጠቀስ ቡድን መሪው ገልፀዋል።

በተጨማሪ በዘርፉ የተከናወኑ የአቅም ግንባታ ተግባራት እና የበርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው ለተገኘው ገቢ ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተጠቅሷል።

ማዕከሉ በ2014 በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቆዳና የቆዳ ምርቶች 10.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ለማግኘት ከታቀደው አንጻር አፈጻጸሙ 78 በመቶ ነበር።

ከ2013 ወዲህ ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ ቆዳዎች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ መፈቀዱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የቆዳ ውጤቶች በአራት ደረጃ የተከፈሉ መሆናቸውም ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here