የእንቦጭ አረም ባለባቸው ሐይቆች አረሙን ከመንቀል ጎን ለጎን በሐይቆች ዳርቻ አገር በቀል የውኃ ውስጥ እፅዋት ሊተከሉ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢኮ ሀይድሮሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዮሐንስ ዘሪሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ፣ በዝዋይ ሐይቅ እና በአባያ ሐይቅ አለ። የውኃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በመሆን የእምቦጭ አረሙን በሰው ኃይል፣ በባይሎጂካል መንገድ እንዲሁም በማሽን በመታገዝ ከማስወገድ ጎን ለጎን ሌላ አማራጭም ተይዟል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የእንቦጭ አረሙን ለማጥፋት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ወንዞች በተፋሰስ መልክ ወደ ሐይቁ የሚመጡ እና ለእንቦጭ አረሙ መራባት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ማዳበሪያና መሰል እንዲሁም ሌሎች ደለሎች ወደ ሐይቁ እንዳይገቡ የማድረግ ሥራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ይህም የእንቦጭ አረሙ ከተከሰተባቸው ከጣና ሐይቅ፣ ከዝዋይ ሐይቅ፣ ከአባያ ሐይቅ በተጨማሪ የእንቦጭ አረሙ ወደ ቆቃ ግድብ፣ አባያና ጫሞ ሐይቅ በሚገኙ በወንዙ ዙሪያ እና ዳርቻ ቄጤማ፣ ደንግል እንዲሁም ሌሎች የአገር በቀል እጽዋትን የመትከል ሥራ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የአገር በቀል እጽዋትን የመትከል ሥራው ከክልሉ መንግሥት እና በሐይቁ ዳርቻ ከሚገኙ የሆቴል ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ጠንካራ ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ ይህም የእንቦጭ አረሙን ለማጥፋት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በሐይቆች ዳርቻ የአገር በቀል እጽዋት መተከላቸው የእንቦጭ አረሙን ለመግታት ከሚኖረው ጠቀሜታ ጎን ለጎን፣ በሐይቁ ውስጥ ለሚኖሩ የአሳ መራባትም ጉልህ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል።
በጣና ሐይቅ በተያዘው ዓመት 2077 ሄክታር መሬት በእንቦጭ አረም ተሸፍኖ እንደነበር እና በአረሙ የተሸፈነውን 1184 ሄክታር መሬት በሰው ኃይል መንቀል መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
አክለውም፣ ዝዋይ ሐይቅ 137 ሄክታር መሬት በእንቦጭ አረም ተሸፍኖ የነበረ ሲሆን፣ 96 ሄክታሩን መንቀል እንደተቻለ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ዓመት እስከ ባለፈው የግንቦት ወር ድረስ የእንቦጭ አረሙን ለማጥፋት ከታቀደው እቅድ አንጻር መቶ በመቶ ማሳካት መቻሉ ተነግሯል።
ዳይሬክተሩ የእንቦጭ አረምን ሙሉ ለሙሉ በሂደት ካልሆነ በስተቀር ማስወገድ እንደማይቻል የሌሎች አገራትም መረጃ ይጠቁሟል ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካሰበችው አንጻር መገምገም ካስፈለገ ከተጠበቀው በላይ አረሙ እየተወገደ ነው ብለዋል።
እንቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ ከተከሰተ 10 ዓመት ያለፈው ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ሐይቁን ለመታደግ ከኹለት ዓመት በፊት ርብርብ ሲደረግ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ስለ እንቦጭ ብዙም ሲነገርና ስላለበት ሁኔታ ሲነሳ አይደመጥም።
የመራባት አቅሙ አደገኛው ነው የሚባልለት እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ማስወገድ ካልተቻለና በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ ከቀጠለ፤ በጊዜ ሂደት ዓባይ ግድብ እንዳይደርስ የሥነ ምህዳር ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ እንቦጭ የመራባት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም በዚሁ ከቀጠለ ዓባይ ግድብ ላይ መድረሱ አያጠራጥርም። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ጣና የዓባይ መነሻ መሆኑን ሲሆን፣ እንቦጭ በአፋጣኝ ካልተወገደ ለአገርም አስጊ መሆኑን ሲያሳስቡ ነበር።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014



