በሚቀጥለው በጀት ዓመት በሰባት ዘርፎች ላይ የጥራት ደረጃ ይወጣል ተባለ

0
1073

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ግብርና እና ምግብን ጨምሮ በሰባት ዘርፎች ላይ የጥራት ደረጃ ለማውጣት ማቀዱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይስማ ጅሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከሚቀጥለው ሐምሌ 1/2014 ወይም ከ2015 በጀት ዓመት ከመጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ በአምራቾችና ኢንዱስትሪዎች በፍላጎት ላይ በመመርኮዝ በሰባት ዘርፎች ላይ የጥራት ደረጃዎችን የማውጣት እና የማሳወቅ ሥራ ለመሥራት እቅድ ተይዟል።

በዚህም መሠረት ግብርና እና ምግብ ዘርፎች፣ ጨርቃጨርቅ እና ቆዳ ውጤቶች፣ ኬሚካል እና ኬሚካል ውጤቶች፣ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፎች፣ ምህንድስና ወይም የግንባታ ዘርፎች ላይ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ያሰባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ከላይ በተጠቀሱ ዘርፎች ላይ ደረጃ አውጥቶ ለኅብረተሰቡ ከማሳወቅ ባሻገር፣ ለአምራቾች ሥልጠና መስጠት፣ የቴክኒክ እና ሌሎች ድጋፎችንም በማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሠራባቸው ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪ ኢንስቲትዩት 210 ያቋቋማቸው የቴክኒክ ኮሚቴዎች ያሉ ሲሆን፣ አምራች ድርጅቶች በሚያመርቷቸው የምርት ደረጃዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ደረጃዎችን አውጥቶ ይፋ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የሚያዘጋጀውን ደረጃም ካረቀቀ በኋላ ለብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት አቅርቦ ከፀደቀ፣ የብሔራዊ ደረጃ ይሆናሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ እስከ አሁን ከ10 ሺሕ በላይ ደረጃዎች ወጥተው የፀደቁ ሲሆን፣ በቀጣይ በጀት ዓመትም አምራች ኢንዱስትሪው የሚወጡ ደረጃዎችን ተንተርሶ ምርቶችን እንዲያመርት እና ሸማቹም ጥራቱን እያረጋገጠ እንዲሸምት ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

የሚወጡ የጥራት ደረጃዎች ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ ባለድርሻ አካላት በአሠራር መስፈርቱ ላይ ተመስርተው ቁጥጥር እንዲያደርጉ እና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶችም ከአሰራሩ እንዲወገዱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመትም በአምስት ዘርፎች 400 የምርትና የአገልግሎት ደረጃዎችን አዘጋጅቶ በብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ማስፀደቁ አይዘነጋም።

ኢንስቲትዩቱ ያስፀደቃቸው ደረጃዎች በምግብና እርሻ፣ በአካባቢና ጤና፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች ፣ በኤሌክትሮ ኬሚካል እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ዘርፎች የተዘጋጁ መሆናቸውም ይታወሳል። ደረጃዎቹ የፀደቁት በ33ኛውና በ34ኛው የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ ነው።

ደረጃዎቹ ሲዘጋጁ አስፈላጊው ጥናትና ዳሰሳ የተደረገባቸው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ለምክር ቤቱ ከቀረቡት 69 አዲስ፣ 125 የተከለሱ እና 206 በማስቀጠል የፀደቁ ደረጃዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎችም ላይ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ ለአብነትም ከአንድ ዓመት በፊት የአካባቢ ንፅሕናን እና የጤና አገልግሎት ላይ ያተኮረ 36 አገር ዐቀፍ የጤና እና ማኅበራት ረቂቅ ደረጃ ማዘጋጀቱም የሚታወስ ነው፡፡

ከእነዚህ መካከል የጤና እና ማኅበራዊ ተቋማት ረቂቅ ደረጃዎች ከዚህ በፊት ያልነበሩ እና አዲስ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ እነዚህ የተዘጋጁ ረቂቅ ደረጃዎችም መሠረታቸውን አገር ዐቀፍ የንፅሕና እና የአካባቢ ጤና ላይ ያደረጉ መሆናቸውንም ማሳወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here