በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ 1.1 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት የአማራ ሕዝቦች ቤተ መዘክር (ሙዝየም) የተሰኘ ግንባታ በሚቀጥለው ወር እንደሚጀምር የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢያለ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል ዋና መቀመጫ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ አፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አካባቢ 16 ሺሕ ካሬ ሜትር በሚሸፍን መሬት ላይ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በሚወስድ በጀት የአማራ ሕዝቦች ሙዝየም የተሰኘ ግንባታ ለመጀመር ታቅዷል ብለዋል።
የሙዝየሙ የዲዛይን ሥራ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው በተያዘው ሐምሌ ወር 2014 እንደሚጀመር እና የክልሉ መንግሥት ለግንባታው የሚውል 60 ሚሊዮን ብር ከተጠናቀቀ በጀት ዓመት እንዲሁም ቀሪው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ደግሞ ከ2015 በጀት ዓመት ላይ እንደሚመድብ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የሙዝየሙ ግንባታ ሥራን አስመልክቶ የክልሉ መንግሥት ባወጣው ጨረታ መሠረት፣ የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት አሸንፎ እንደተረከበ እና ግንባታው በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደታቀደ ተነግሯል።
ኃላፊው አክለውም፣ የሙዝየሙን የግንባታ ሂደት አስመልክቶ የአማራ መንገድ እና ሕንፃ ዲዛይን ቁጥጥር ባለሥልጣን የማማከር እና የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል ብለዋል።
የሙዚየሙ የግንባታ ሂደት ተሠርቶ ሲጠናቀቅ፣ በክልሉ ውስጥ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ገላጭ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖታዊ እና አጠቃላይ የሕዝቡ የሆኑ ቅርሶች በተደራጀ መንገድ ለጉብኝት እንደሚቀርቡ ኃላፊው አመልክተዋል።
ይህ ሙዝየም ሲጠናቀቅ፣ በክልሉ ካሉት ብቻ ሳይሆን በአገር ዐቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው ሙዝየም ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ተናግረዋል።
ለጊዜው ቁጥሩ ባይታወቅም የሙዝየሙ ግንባታ መጀመሩ ለበርካታ የቀን ሠራተኞች፣ በግንባታ ሥራ ላይ ለተሰማሩ እና ለሌሎች ሰዎችም የሥራ እድል ይፈጥራል ነው የተባለው።
በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በቀጣይ ወር የግንባታ ሥራው እንደሚጀመርለት የተነገረው ይህ ሙዝየም፣ ከአምስት ዓመት በፊት ይጀመራል ተብሎ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦለት ነበረ። ሆኖም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በክልሉ ተፈጥረው በነበሩ የፀጥታ ችግሮች እና ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ መሆኑን ተከትሎ በበጀት እጥረት ምክንያት የሙዝየሙን ግንባታ በተባለው ጊዜ መጀመር እንዳልተቻለ ተነግሯል።
በአማራ ክልል የሚኖሩ ሕዝቦች የክልሉን ሕዝብ ማንነት የሚገልፅ ሙዝየም እንደመሆኑ መጠን የሙዝየሙ ግንባታ እንዲጀምር በተደጋጋሚ ቅሬታ መነሳቱን ተከትሎ፤ የሕዝቦችን ጥያቄ ከመፍታት ጎን ለጎን የሥራ ማስኬጃውን በጀት ማመቻቸት በመቻሉ በሚቀጥለው ወር የግንባታ ሥራውን ለማስጀመር የታሰበ ነው።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በክልሉ በሕወሓት ቡድን ጥቃት ተፈፅሞባቸው የነበሩ እና ለጉዳት የተጋለጡ ቅርሶችም የጥገና ሥራ እንዲከናወንላቸው እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል። ለአብነትም በደሴ ከተማ የሚገኘው የመርሆ ግቢ በሕወሓት ቡድን ጉዳት ደርሶበት እንደነበር እና ይህ ሙዝየምም የጥገና ሥራ እየተደረገለት ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014



