የሰው ልጅ ከልደቱ ጀምሮ ውድድርና ፉክክር ውስጥ አድጎ ይህን ዓለም ይሰናበታል። ከምግብ ፍለጋና ምርጫ አንስቶ፣ ሀብት ለማከማቸትም ሆነ ለዝናና ለሥልጣን እርስ በርሱ የሚወዳደርና የሚፎካከር ሰው ወደ ግጭት ማምራቱ የማይቀር ነው። በየትኛውም መስክ ቢሆን ይህ የፉክክር ባሕሪ የማይቀር እንደመሆኑ የሰው ልጅ በመላ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ እንደሚኖርበት ይታመናል። ታዲያ ይህ የማይቀር ሂደት እንደሌለ ቆጥሮ ተጎጂ ከመሆን አልያም አላስፈላጊ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከመዳከር አስቀድሞ መንስኤውም ሆነ ማክሸፊያው ላይ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በድሉ አበበ በዚህ ጽሑፋቸው እንዲህ ያስረዳሉ።
በሕይወት ስንኖር ከሚገጥሙን ሚሊዮን ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ለሕይወት ዘመን ግብና ስኬት እሽቅድምድምና ፉክክር ነው። እንኳንና ታላቁ የሰው ልጅ የዓለም ፍጥረታት በሙሉ የማይቋረጥ ፉክክር ላይ ናቸው። ሰማይ ምድሩ፤ ሰው አራዊቱ፤ እጽዋቱ ሁሉ ዓለም ያላት ሀብት የተመጠነና የተቆጠረ ነው፤ በሰው ፊት። በመሆኑም የሰው ልጅ ያንን ያለውን የዓለም ሀብት ለማወቅ፣ አውቆም ቀድሞ ለመጠቀም ይጣጣራል። ይወጣል ይወርዳል። ይቆፍራል፤ ይለፋል።
አለቃ ዘነብ “የዚህን ዓለም ስር አገኛለሁ ብዬ ቆፈርኩት። ብለው ብቆፍረው ስሩ እግዚአብሔር ነው።” ብለዋል /ቃል በቃል አይደለም/። ስለዚህ ሰው የተሰጠውን አእምሮ ተጠቅሞ ሁሉን ለማወቅ ይጥራል፤ሁሉን ማወቅ ባይቻልም ቅሉ። የዓለምን፤ የአገሩን የመንደሩን ሀብት ለማወቅ ብቻ አይመስለኝም የሰው ልጅ ይሄን ያህል የሚደክመው፤ ካወቀም በኋላ ለራሱና ለቤተሰቡ፤ ለአገሩና ለዓለም ጥቅም ሊያውለው እንጂ። መብላት መጠጣቱ፤ መማር ማጥናቱ፤ መልበስ ቤት መገንባቱ ሁሉ ለዚህ ነው በዚህ ምድር።
በዚህ መሃል ግን ዓለም ብዙ ዓይነት ሕዝቦችና መልክ ስላሏት ብዙ ውድድሮች ይኖራሉ። እኛም የዚያው አካል ነን፤ ተወደደም ተጠላም። ተወዳዳሪዎቹ ራሳቸው አንዳንድ ጊዜ ከማን ጋራ እየተወዳደሩ እንደሆነ እስካያውቁና ግራ እስኪገባቸው ድረስ ውድድሩ ይጦፋል። የማናውቃቸውም የምናውቃቸውም ውድድሮች አሉ ማለት ነው። ውድድሮቹ በግልም በቡድንም፤ በእድሜ እኩያነትም ያለእኩያም፤ በተለያዩ ጾታዎችም፤ በተለያዩ ብሔሮችም፤ በተለያዩ አገሮችም፤ በተለያዩ ምክንያቶችም፤ በተለያዩ ዓይነቶችና ስልቶች መካከል ሊሆን ይችላል። አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ይሁኑ፤ ዘመናዊ የሕይወት ውድድር ላይ ነን፤ ሁላችንም። መልኩ ቢለያይም!
የምንወዳደረው በአጠቃላይ ዓለም ዛሬን ለማደር ጥሪት፤ ነገን ለማቀድ ደግሞ ሀብት ስለሚያስፈልጋት ነው። መንግሥታትም ሕዝቦቻቸውን አውለው ለማሳደር ሀብት ያስፈልጋቸዋል። በተጓዳኝ ደግሞ አንድ ቦታ ላይ አንድ ሀብት ሲበዛ፤ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ያው ሀብት ያንሳል። ሀብት ደግሞ በባህሪው አላቂ ነው። እንኳን ሀብቱ ተጠቃሚው የሰው ልጅ ራሱም ያልፋል። በመሆኑም፣ በዓለም ላይ ያለው ሀብት ለዓለም ሕዝብ ዐይን ሲታይ ደግሞ እጅግ ጥቂት ነው።
ይሄን ጥቂት ሀብት የሚፈልግ፤ ፈልጎም ለማግኘት የሚያቅድ፤ የሚያልም፤ የራሱ ለማድረግ በስውርም በይፋም፤ በውጭም በውስጥም የሚያቅድ፤ የሚለፋ አካል አለ። ስለዚህ ብዙ አክተሮች ይህን ሀብት ቀድሞ የራስ ለማድረግ፤ አድርጎም የራሱና የታሪኩ አካል ለማድረግ ይተጋል። ይሄም ሌላ ሃቅ ነው መዋጥ ያለበት። እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ መከራውን ምን አመጣው ታዲያ ካልን፣ ውድድሩ ፍትሃዊና እኩልነትን የተጫነው ስላልሆነና ጉልበት ደግሞ በእጅጉ የተጫነው በመሆኑ ነው።
ለምሳሌ፣ ዓለም የውድድር መድረክ ናት ይባላል፤ እኛም ተወዳዳሪዎቹ። ውድድር የተፈጥሮ እውነታ ነው፤ ይሄንን እንቀበል፤ እንመንና እንዘጋጅም። እንደ ሰላምና ደኅንነት (peace and Security) ባለሞያዎቸ ገለጻ ከሆነ፣ የምንወዳዳረው በአብዛኛው ለሦስት ጉዳዮች ነው። እነዚህም ከበጣም ጥቂት እስከ ቢሊዮን ያለውን የአእምሮ ሀብትን ጨምሮ ለሀብት ሲሆን፤ ኹለተኛው ደግሞ ሥልጣን (ከቀበሌ ሹምነት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነት) ለመቆናጠጥ ነው። ሦስተኛው በ‹ባዮሎጂካል› ምክንያቶች ነው።
ወድድሩ የተለያዩ ውጤቶችን ይዞ መምጣቱም ሌላ መዋጥ ያለብን ሃቅ ነው። ውድድሩ ተዋናዮች (አክተርስ) አሉት ብለናል፤ ቀደም ብለን። እነዚህም ከጊዜ የቀደሙ፤ በጊዜው ለመፎካከር የቋመጡ ወይም ለነገ አቅደው ያስቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። በግዜ ከለካነው ደግሞ እጅግ ፈጣኖች፤ ፈጣኖች፤ የዘገዩና በጊዜው ያላቀዱም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ተወዳዳሪዎቹ። ግጭቱ ይሄንን ዓይነት መልክም ይኖረዋል ማለቴ ነው።
በሌላም መልኩ ደግሞ ተዋናዮቹ ልምድ አልባ፤ መካከለኛና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ ይችላል። በሂደት የጊዜን ግጭት አክሎ እየተጓዘ፤ በተዋናዮቹም ማንነትም ላይ ይመሠረታል ማለት ነው። ከለጠጥነውም ከውጭ አገርና ከአገር ውስጥም፤ አንድም አብረው አልያም ተለያይተው ሊሆን ይችላል። ግባቸውም አንድ አልያም ብዙ። በአንድ ታክቲክ ወይም በብዙ ታክቲካቸውና ቴክኒካቸውም ለአንድ ወይም ለብዙ ግብ መሰለፍ ሊሆን ይችላል። ስትራቴጂም አያጡም።
ሦስተኛ በተወዳዳሪዎች እውቀትም እንደቀደመው ይወሰናል ማለት ነው። በተጨማሪም የምንወዳደርለት የሀብት ዓይነትም እንዲሁ የፍልሚያውን ሁኔታ ሊወስን ይችላል። ለዳይመንድና ለመሬት እኩል አንወዳደርም። የተወዳዳሪዎችን ታሪክና ሕዝብ፤ ስልትና ማንነት ደግሞ የውድድሩን አድማስ ባልተገመተ መልኩ ሊቀይረው ይችላል። አንድ እንጨምር እስቲ ደግሞ፤ ይሄን የሚያቀላጥፉ መካከለኞችን መዘንጋት በዚያው አግባብ አይደለም፤ የውድድሩ አንድ አካል ናቸውና!
ለምሳሌ፦ እስቲ ወደ እኛ መስሪያ ቤት እንውሰደው። አንድ ባልደረባ አለን እንበል። የምንሠራለት መሥሪያ ቤት ደግሞ አንድ የጋራ ራዕይ ይኖረዋል። ስለዚህ እኛም ባልደረባችንም የሚከፈለን አንድም መሥሪያ ቤቱ እንዲሳካለት በሂደቱ ላይ ባለን በጎ አስተዋጽኦ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መሥሪያ ቤት ሙሉ በሙሉም ባይሆን ባሳካው የሚታይና የሚቆጠር ስኬት ላይ ተመሥርቶ ነው። በጋራ መሥራት ያው የከረመ ልምድ ስለሆነ፤ ባልደረባችን በማናውቀው ምክንያት የዐይን ቀለሙ ይቀየራል፤ ከመልካም መልካም ወዳልሆነ።
እኛ የምናውቀው ነገር የለም። በግል የተሰጠንን ሥራችንን እየሠራን ነው። ከሱም ጋራ በጋራ የተሰጠንን ሥራ አብረን እየሠራን ነው ብለን እናስባለን። በጎ መሆንና በኅብረት መሥራትን፣ ለመሥራትም ለማየትም ያልታደሉ አሉና ሥራ ትተው ሴራ ይወጥናሉ። እኛ ባናውቀውም ውድድር ውስጥ ገባን ማለት አይደለም? ውጤቱ ምናልባትም በጎ እንደሆነኮ አጥተነው አይመስለኝም። ይቀጥላሉ እናም የዕይታ ግርዶሻቸውን መከላከል ይሳናቸዋል።
እኛ ሥራ እየሠራን እንደሆነ ነው የምናውቀው። ምናልባትም በብዙ መስፈርት ከታየ ከእነዛ ሰዎች በታች ነን የምንል፤ እንብለጥ ያላልን ለፍቶ አዳሪ! እነሱ ግን በቀጥታ ጽንፍ የወጣ ውድድር ያደርጉታል። ኅብረቱ አንድ ላይ መብላቱ፤ አንድ ላይ መሥራቱ፤ ለአንድ ዓላማ መሰለፉ ወደ ፉክክር ያመራል። መወዳደሩምኮ ባልከፋ! ጭራሽ ብሶበት ሴራ ይጎነጉናል።
መሥሪያ ቤት ውስጥ ለራስና ለመሥሪያ ቤት ድል፤ ስኬት እንዲሁም ለአርዓያነት መወዳደርና መትጋት ማስፈለጉ እሙን ነው። ነገር ግን ውድድሩ ከመካከለኛው ደረጃና አግባብ ካለው አካሄድ አፈንግጦ ወዳልተገባ አቅጣጫ ሲያመራ፣ አሉታዊ ውጤት ያመጣል። በዚህም የሚጎዱ ብዙ ሰዎች መኖራቸው አይቀርምና በመጠኑ በአግባቡ መወዳደር ያስፈልጋል።
ቀደም ብለን እንዳልነው ግጭትና ውድድር አይቀሬ ተፈጥሮአዊ ሁነት ነው። አልፎ አልፎም ውድድር ሳይሆን መልካምነት ያነሰው ያልተገባ ፉክክር ይወለዳል። የሥራ ሰዎች ሴራ ይከብዳቸዋል፤ ለሴራ ሳይንስ ርቀት አላቸውና አይገባቸውም። የልምድ ጉዳይ ስለሆነ ማለት ነው። እኛ ባላወቅነው እነሱ በተካኑበት የሴራና ጥሎ ማለፍ ሞያ መሃል ግጭት ይፈጠራል ማለት ነው። እዚህ ድረስ አለማወቅ ግን የፈጣሪን የልብ ንጽህና ስጦታ ይሻል። ከዚያም ያው ልብ ያላልነው፤ ያልገመትነውም ቢሆን ሰው ነንና ዘው ብለን አስበንም ሳናስብም፤ አውቀንም ሳናውቀውም፤ ሳንገምትም መግባታችን አይቀርም።
ወደ ፉክክር ስንገባ ግን ምርጫችን እንዳይደገም ለማሳፈር፣ ንጽህና ፍራቻ እንዳልሆነ ለማሳየት፣ እኩልነታችንንም ለማሳየት፣ ለወደፊቱ እንዲማር፣ ሌላ ልምድ ያለው ከምድረ ገጽ የሚያጠፋው እንዳይጎዳው እንዲሁም መብታችንን ለማስከበርና ለሌሎችም ቢሆን እላለሁ። እነዚህም የነገ የሕሊና ጸጸት የማያስከትሉ ጉዳዮች ቢሆኑ እመርጣለሁ። ክፋት ሲያሸንፍ የተፈጥሮ ፍትህና እውነት ይዛባልና!
የውድድር ሰዎች ሆይ! ውድድር አይቀሬ ነውና ሁሌም ቀድሞ መጠንቀቅ፤ በንቃት መከታተል፤ ሥራን ማክበር፤ ራስን ማክበር፤ ሌላውንም ማክበር፤ የድርጅትንና የአገርን ሕግና ሥርዓት ማክበር እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉንም ቢቻል ልብን አስፍቶ ማቀፍ ቢቻል የአባት ነበር። እንዲህ እንዲሆን ልቦች የልብ ትክሻቸው ዘመም ይልባቸዋል እንጂ።
እኔ እንደዚህ የታደሉ፣ ነገር ዓለሙ የማይገርማቸው እንዲያውም ለሚያደርጉት የሚያዝኑና የሚጸልዩ አውቃለሁ። እነዚህ መልካምነትና የሰውን ልጅ ድካም በተሻለ የተረዱ ናቸው። ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያዊያን ካደግንበት ሰፈር ፍቅር፤ አብረን ካደግናቸው ጓደኞቻችን ፍቅርና መስዋዕትነት፤ ካሳደጉንና ካስተማሩን የተለያዩ ሰዎች ማንነትና ሃይማኖት አንጻርና ከባህል ሃይማኖት አኗኗርና መሰናሰል አኳያ ስናየው ልባችን ሰፊ ነው ማለት እንችላለን። ጥቂት ልቦቻቸው ጠበው፤ ራስ ወዳድነት ተጭኗቸው፤ የተጫነባቸውንም መግራት አቅቷቸው፤ ልምድም ወደ ግራ መርቷቸው ውድድሩን ወደ ከፋ ግጭት ይወስዱታል እንጂ።
ግጭትም ተፈጥሯዊና ፈርጀ ብዙ ነው፤ መከሰት ያለበት ቢሆንም ተወዳድሪዎቹ ራሳቸውን ስለ መግራት ማሰብ ግድ ይላቸዋል። የውጭም የውስጥም ምክንያቶች የውድድርን ሂደት ቢወስኑትም የኛ የውስጥ ስሜትና ታግሎ የማሸነፍ ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ተወዳዳሪም ሆኜ እኔ በግሌ አሁን አሁን ስለሰው መልካም ያልሆነ አስተያየት ሲመጣብኝ እንዲህ እላለሁ፤
‹‹ወንድሜኮ እኔን ሊጠላ አይችልም፤ ይወዳደረኛል፤ ይፎካከረኛል እንጂ። ምናልባትም በዚያች ሊፈርድ ባሰበበት ቅጽበት በአሉታ ዐይን ስላየኝ ወይም ስላላወቀኝ ወይም የሕይወት መልኮች ስላልገቡት ወይም ወይም እንደኔ ዓይነት ሰው በዕድሜው ዓይቶ ሰለማያውቅ ወይም ስላልተማረ ወይም ስላልጸና ወይም መልካም ምግባር ስለሌለው ወይም ሰው መጉዳትን እንደ ሞያ ሳያውቀው ወስዶት ድንገት እንደ ደራሽ ጎርፍ ወስዶት ወይም ሃይማኖትና ባህል ያልገሩት ማንነት ባለቤት ስለሆነ ወይም ሁሉን የመቆጣጠር የግል አባዜ ኖሮት ካልሆነ በቀር በክፉ አይጣላኝም።››
በተጨማሪም፤ ከውድድር በላይ በሆነ መልክ ሰው ሰውን በክፉ ለማየት ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ በውድድር መሃል። በበጎ ለመረዳት መጣሩ ግን ላንተም ለሌላውም በጎ ነገርን ይወልዳልና እየተጎዳህም ቢሆን መልካም ሁን። ራስህንም ደጋግመህ ጠይቅ። ለራስህ ጊዜ ስጥ። ክፉ ዕይታህን ለራስህም ደግመህ ባትነግረው እመርጣለሁ። በሐሳብ ቀረ ማለት አይደል?
አሁንም ልምምዱን ቀጥልና ቢብስም ለሌላ ሰው ላለመግለጽና ላለማውራት ጥረት አድርግ። በደሉ ብሶ ከፈጠጠም የምታማክራቸው ምስጢር ጠባቂዎች መሆናቸውን ለይ። ስታማክርም ወደ መልስና ሌላ ጉዳዮች መሄድ አለመሄድን ደጋግመህ አስብ። በወዳጆች መሃል መቅረት የሚችል ጉዳይ ሊሆን ይችላልና። ከዚያም ስሜትን ያሸነፍክ ከሆንክ ቢቻልህ በጉዳዩ ዙሪያ በግልጽ ለመወያየት አትፍራ። ክፉ አድራጊ ቀባጣሪ ቢሆንም ቅሉ።
ወደ ተግባር ለመግባት ደጋግሞ ማሰብ ደግሞ የበለጠ ይሻላል። ጊዜ፤ ቦታና ሁኔታ ባልተጠበቀም መንገድ ሊቀየሩ ይችላሉና። ደግመህ እንዲህ በል:- እኔ ነኝ ወይስ ዐይኔ ነው። ማንነቴ ነው ወይስ አይደለም? ባክህ ይቅር በለኝ ፍጡርህንኮ ባልሆነ ዐይን አየሁት። ለምን በበጎ ዐይን ላየው አልፈቀድኩም? ያንተን ፍጡር ደግሞ ማድነቅና ማክበር እንጂ እንዲያ ማየት በራሱ ኃጢአት አይሆን ይሆን? ይሄ ደግሞኮ ድሮ ያልነበረኝ ጸባይ ነው። የሰው ልጅ እንኳን ለክፋት ለመልካሙም ጊዜ አጥሮታልኮ፤ በተለይ በዚህ ዘመን።
በአጠቃላይ ካየነው ደግሞ አንድም በኔ ጥቂት ጥፋትና እሷን በማግነን፣ ሁለትም በሱ እጅግ የገዘፈ የዕይታ ብዥታና በራሱ ነው እንጂ እግዚአብሔርኮ ጥላቻን በልቦናዎቻችን ውስጥ አልፈጠረም። ምክንያቱም ሰውን ሙሉ በሙሉ ማወቅ አይቻልም። እንዲያው ብቻ በገባን ልክ እንፈርጃለን እንጂ። “የእጁን ይስጠው” ብሎ ማለፍም ምርጫ ነው፤ ትክክለኛ ምርጫም ባይሆን። አልወዳደርም ካልክ ግን አለመወለዱ፤ አለመኖሩ ሳይሻል ይቀራል? የውድድር ሰዎች ሥነ ልቦና እንዲህ ከዚህ በፊት እንደገለጥነው ቢሆን የሚደፈጠጡና በመሃል የሚጎዱትን እንቀንሳለን ብዬ አስባለሁ።
ለጥቆም በግጭቶቻችን ወቅት እንበልና አንዱ አካል ምንም አያውቅም፤ ለግጭቱም ምክንያት አይደለም፤ በተግባርም የለበትም፤ አይገምትም አይተውንም፤ ምናልባትም ጉዳዩን አያውቀውም፤ ብዙም የለበትም። በዚህ ምክንያትም አይፈራም አይሰጋም። ከግጭቱ ስበት ግን ላያመልጥ፤ በግጭቱ ውጤትም ሊጎዳው ይችላል፤ ለጊዜውም ቢሆን።
እኔ በተፈጥሮ ሕግ አምናለሁ። ተፈጥሮ ባላንስ (balance) ታደርጋለች ብለን እናምናለን። ጎጂ እንደጎዳ የሚቀጥልበትን ዕድልን ተፈጥሮ ትነፍጋለች። ሰማይ ምድሩ የሚደንቅ ያልተነገረ የተፈጥሮ ቀመር እንዳላቸው እናምናለን። ሰማይን ቀና ብለን ምድርን ጎንበስ ብለን ስናይ ሕጉ በተሻለ ይገባናል። ክፉ ያሰቡ ጭንቅላቶች የበለጠ ክፉ ይጠብቃቸዋል ብለን እንገምታለን። በረጋ ሕሊና ያልተወሰኑ ውሳኔዎች የረጋ ሕሊና ሲመዘኑ ቀለው ይገኛሉ። በክፉ የተራመዱ እግሮች፤ ክፉ መሰናክሎች አያጧቸውም። አሳዳጅነት ተሳዳጅነት ይጠብቀዋል።
ሁሉም የዘራውን ማጨዱ የሰርክ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ሁላችንንም በሚገጥሙን መልካም ያልሆኑ ነገሮች ውስጥ ጥቂት እጃችን ሊኖር ቢችልም ብዙው የነርሱ ነው፤ ስለዛ እጅ የሚያገባን አይመስለኝም። አልሞ አቅዶ ለመጣም አልሞ አቅዶ የሚመጣ ምናልባትም ከርሱ በላይ የተዘጋጀ ጠላት ሊገጥመው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአተኛን ኃጢአቱ ራሱ ታሳድደዋለች” ይላልና!
እንዴት፤ በማን በኩልና በየት በኩል እየተወዳደርንና እየተሸናነፍን ማሰብ ስለማንፈልግና ስለማናተኩርም ነው እንጂ፤ አገር ምድሩ ውድድር ላይ ነው። ያንን ለመረዳት ጊዜም ሁኔታውም አልፈቀደ ይሆናል እንጂ። ስለዚህ ወገን…ኑ እንወዳደር፤ እንፎካከር። ግጭት ይጥፋ ባንልም መጠፋፋቱን እናሳድረው፤ አያኗኑርምና!
የጽሑፉን አዘጋጅ በድሉ አበበን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015



