የመማሪያ መጻሕፍት ባለመቅረባቸው በመማር ማስተማር ላይ ክፍተት ተፈጥሯል ተባለ

0
989

በመላው ኢትዮጵያ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁትን መጻሕፍት መምህራን እና ተማሪዎች ባለማግኘታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ ክፍተት መፍጠሩን መምህራን ገለጹ።

ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን መማሪያ መጻሕፍት ማዘጋጀት የክልል ትምህርት ቢሮዎች ኃላፊነት ሲሆን፣ መጻሕፍቱ ተዘጋጅተው እንደተጠናቀቁና ከህትመት በኋላ ለተማሪዎች እንደሚደርሱ መነገሩ የሚታወስ ነው። ተዘጋጅተዋል  የተባሉት የመማሪያ መጻሕፍት ግን ታትመው ለተማሪዎች እንዳልደረሱ፣ በዚህም በትምህርት ሂደቱ ላይ መስተጓጎሎች እንደተፈጠሩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህራንና የተማሪ ወላጆች ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት መሠረት ቸሩ፣ እስካሁን ድረስ ክፍል ውስጥ ተማሪዎቻቸውን በሚያጽፏቸው ማስታዎሻዎች ላይ የተደገፈ ትምህርት እያስተማሩ እንደሆነና ተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍት አለማግኘታቸው በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ መሸፈን ያለባቸውን ትምህርት ያህል እንዳልሸፈኑ የተናገሩት መሠረት፣ ለተማሪዎቻቸው የቤት ሥራ መስጠትና ቤታቸው አጥንተው እንዲመጡ ማድረግ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ቤተሰብ የሆኑት በረከት ውድነህ ደግሞ፣ ‹‹ወላጆቻችሁ በፍላሽ ዲስክ መጽሐፍ ይውሰዱላቸሁ›› እንደተባሉ ወንድማቸው እንደገለጸላቸው ተናግረዋል። ይሁንና መጽሐፉን በሶፍት ቅጂ (soft copy) ለመቀበል ስልክ ይዘው ቢሄዱም መጽሐፉን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት አራተኛ ክፍል የሚማር ልጅ እንዳላቸው የተናገሩት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ወላጅ፣ በተመሳሳይ በሶፍት ኮፒ እንጂ የታተመው መጽሐፍ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል። ያገኙትን ሶፍት ኮፒ መጽሐፍ ፕሪንት በማድረግ ልጃቸው እንዲማርበት ያደረጉ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪ ወላጅ አብዛኛው ተማሪዎች ይህንን ማድረግ ስለማይችሉ ያለመጽሐፍ እየተማሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ትምህርት ከተጀመረበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ተማሪዎች በመማሪያ መጽሐፍ ታግዘው ቢማሩ መልካም እንደሆነ የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን ለማስጠናት መጻሕፍቱን ማግኘት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት የሆኑት ማህሌት ግርማ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መማሪያ መጽሐፍ ክፍል ውስጥ ለማስተማር እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው፣ መጽሐፍ ባለመኖሩ ምክንያት መማር ማስተማሩ ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በሶፍት ኮፒ መጻሕፍት እንዳሉ የተናገሩት ማህሌት፣ ይህን አማራጭ መጠቀም የሚችሉ ተማሪዎች ብዛት አናሳ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች አራቱን የቋንቋ ክህሎቶቻቸውን እንዲያዳብሩ፣ ከክፍል ውጭም በቤታቸው እንዲያጠኑ መጻሕፍት ወሳኝ ናቸው ያሉት ማህሌት፣ መማሪያ መጻሕፍት በጊዜ መቅረብ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለመቀበል አዲስ ማለዳ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ እንዲሁም ለፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በጽሑፍ መልዕክት ጥያቄዎቿን ልካ በስልክ መልስ ለመቀበል ብትሞክርም፣ የሥራ ኃላፊዎች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ባለመመለሳቸው እንዲሁም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቢሯቸው ባለመገኘታቸው ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2015 ሙሉ በሙሉ፣ በዘጠኝና ዐስረኛ ክፍሎች ደግሞ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በከፊል ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ በአስራ አንደኛ እና አስራ ኹለተኛ ክፍሎች ደግሞ ነባሩ ሥርዓተ ትምህርት እስከ 2016 ድረስ ተግባራዊ እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here