ብዙ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ሊሻሻል መሆኑ ተገለጸ

0
2832

ከ17 ዓመታት በኋላ በ2012 የተሻሻለውና አሁንም በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 1186/2012 ሊሻሻል መሆኑን አዲስ ማለዳ ከገንዘብ ሚኒስቴር ምንጮቿ ሰምታለች።

የኤክሳይዝ ታክስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁና በእቃ እና አገልግሎት ላይ ከሚጣሉ ታክሶች ምድብ ውስጥ የሚገኝ ታክስ ሲሆን፣ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎችና አገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የሚጣል ታክስ ነው።

በ2012 አዋጁ ሲስተካከል በምርቶችና እቃዎች የመሸጫ ዋጋ ላይ መሠረት ተደርጎ በሚሰላ ሂሳብ፣ ከአገር ውጭ በሚገቡ መኪናዎች ላይ ከ5 በመቶ እስከ 405 በመቶ፣ በሲጋራ ላይ 30 በመቶ፣ በታሸገ ውሃ ላይ 10 በመቶ ታክስ መጣሉ ሲታወስ፣ አምራቾችና አስመጪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ሲያሰሙበት ተደምጧል። አዋጁ ገና በመሻሻል ላይ እያለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በርካታ ጥያቄዎች የሚቀርብበት ነው።

የኤክሳይዝ ታክስ ዋና ዓላማዎች ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ፍጆታ መቀነስ፣ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት እቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ እንዲሁም በአካባቢ ደኅንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች አጠቃቀም መቀነስን ያለመ መሆኑን መንግሥት ሲገልጽ ነበር። ቢሆንም በአዋጁ መሠረት ኤክሳይዝ ታክስ እንዲቆረጥባቸው የተወሰነባቸው ምርቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቧል።

እነዚህ ጥያቄዎች ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እንደቀረቡ የገለጹት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ለቀረቡት ጥያቄዎች የተናጠል መልስ እንደማይሰጥ ገልጸው፣ በአጠቃላይ አዋጁን ለመከለስና ለማሻሻል እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህ ማሻሻያ መቼ ይጠናቀቃል የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ምንጩ ማሻሻያው እየተሠራበት እንደሆነ ከመናገር ውጭ በዚህ ቀን ያልቃል ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል።

በተያያዘም፣ በ15 የውሃ አምራች ፋብሪካዎች ላይ በተካሄደ ጥናት በፋብሪካዎቹ ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ተጠቃሚ ላይ (ግማሽ ሊትር ውሃ ላይ እስከ አንድ ብር የሚደርስ፣ በአንድ ሊትር ውሃ ላይ እስከ አንድ ብር ከሀምሳ ሳንቲም የሚደርስ፣ በኹለት ሊትር ውሃ ላይ ከኹለት ብር የሚያልፍ)፣ የዋጋ ጭማሪ እንዳስከተለ የውሃና ጁስ አምራች ፋብሪካዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አሸናፊ መርዕድ ገልጸዋል።

በዚሁ ጥናትም ኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ በምርት ብዛት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳመጣ አረጋግጠናል ያሉት አሸናፊ፣ ይህ ታክስ ቢነሳ መንግሥት በኤክሳይዝ ታክስ ምክንያት ያገኝ የነበረውን ገቢ አጠቃላይ በሚጨምረው የምርት መጠን ማካካስ እንደሚችል ተናግረዋል።

ይህንን የጥናት ውጤት በማያያዝ ለገንዘብ ሚኒስቴር ኤክሳይዝ ታክስ እንዲነሳልን ጥያቄ አቅርበናል የሚሉት አሸናፊ፣ በጥናቱ እንዲሁም በጥያቄያችን ዙሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረግነው ውይይት አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል ብለዋል። በዚህም ምክንያት በቅርቡ የኤክሳይዝ አዋጁ እንደሚሻሻል እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ሊሻሻል ነው ቢባልም፣ የታክስ ቅናሽ እና መነሳትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንደማይሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጫችን የገለጹ ሲሆን፣ በአጠቃላይ አዋጁን እንጂ በተመረጡ ምርቶች ላይ ብቻ ያማከለ ማሻሻያ እንደማይደረግ አረጋግጠዋል።

የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 ኤክሳይዝ ታክስ ስሌት መሠረት የሚያደርገው የማምረቻ ወጪን መሠረት በማድረግ የነበረ ሲሆን፣ በ2012 የጸደቀው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 1186/2012 ደግሞ በምርቶች የመሸጫ ዋጋን መሠረት ያደረገ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here