የነዳጅ አዳዮች የትርፍ ህዳግ በቅርብ ጊዜ እንደሚሻሻል ተገለጸ

0
1803

በሊትር አንድ ብር ከ25 ሳንቲም ትርፍ ተጠይቋል

ነዳጅ አዳዮች ያቀረቡት የትርፍ ህዳግ ማሻሻያ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ተሰጥቶት በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ እንደሚደረግ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ለዓመታት በሊትር 23 ሳንቲም ሆኖ በሥራ ላይ የቆየውን የነዳጅ አዳዮች ትርፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። ማኅበሩ ጥያቄውን ያቀረበው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን፣ የቀረበው የትርፍ ህዳግ ማሻሻያ ጥያቄ የትርፍ ህዳጉ አሁን ካለበት ወደ አንድ ብር ከ25 ሳንቲም ከፍ እንዲል ነው።

ጥያቄው የቀረበለት ባለሥልጣኑ በዘርፉ ያለውን ችግር ተገንዝቦ በጥናት ላይ የተመሠረተ ማሻሻያ ለማድረግ ሲሠራ መቆየቱን የነዳጅና ኢነርጂ ባለ ሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሔኖስ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ነዳጅ አዳዮች የሚያገኙት ትርፍ ዝቅተኛ መሆኑን እና ሊሻሻል የሚገባው መሆኑን ባለሥልጣኑ ተቀብሏል። ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ባለሥልጣኑ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትርፍ ሕዳጉ ማሻሻያ ይደረግበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር የተወሰነለት የትርፍ ህዳግ አለመሻሻሉ ለሥራውና ለዘርፉ ችግሮች መባባስ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል አፈወርቅ ጥላሁን ጠቁመዋል። የትርፍ ምጣኔው አነስተኛ መሆን፣ ነዳጅ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዳይሸጥ በማድረግ ኅብረተሰቡ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም አፈወርቅ ይናገራሉ። ነዳጅ አዳዮች አሁን ባለው የትርፍ ወሰን መሠረት ከአንድ ቦቴ ነዳጅ 10 ሺሕ ብር ነው የሚያተርፉት። ይህም እየጨመረ ካለው ተጓዳኝ ወጪአቸው አንጻር ፍጹም አዋጭ አልሆነም ማኅበሩ ይገልጻል።

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላኛው የማኅበሩ አሥራ አስፈጻሚ አባል ኤፍሬም ተስፋዬ፣ የትርፍ ምጣኔው አነስተኛ መሆን፣ የዘርፉ ባለሀብቶች እንዳይበረታቱ እና በሒደትም ከገበያው እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ይላሉ። ለዚህም እንደማሳያ የሚያነሱት ኢትዮጵያ ካሏት 1 ሺሕ 200 ገደማ ማደያዎች በሥራ ላይ ያሉት አንድ ሺህ የማይሞሉ መሆናቸውን ነው።

ኤፍሬም እንደሚሉት፣ እንደ ኬንያና ዩጋንዳ ያሉ በሕዝብ መጠን ከኢትዮጵያ የሚያንሱ አገራት ዕጥፍ የነዳጅ ማደያዎች አሏቸው።

በኢትዮጵያ ያለው የትርፍ መጠን አነስተኛ በመሆኑ የግል ባለሀብቱ በየአካባቢዎች ማደያዎችን በመገንባት መዋዕለ ንዋዩን እንዳያፈስ ማድረጉንም የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ ነዳጅን በውድ ዋጋ ከውጪ የምታስመጣ እንደመሆኗ የተጋነነ ትርፍ መሆን ባይኖርበትም፣ በአንጻሩም ቢሆን አትራፊ አለመሆኑ የነዳጅ ማደያዎች እንዳይስፋፋ በማድረጉ ግን ሕጋዊ ነጋዴዎች ሊያተርፉ ከሚችሉበት ብዙ ዕጥፍ እያተረፉ ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ ለሚሸጡ አካላት ሁኔታው በር ከፍቷል ሲሉ ይናገራሉ።

የነዳጅ ማደያዎች አለመስፋፋት ከዘርፉ ትርፋማነት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን የሚያምኑት የነዳጅና ኢነርጂ ባለ ሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሔኖስ፣ በትርፍ ምጣኔው ማነስ ማደያዎች ባልተዳረሱባቸው አካባቢዎች ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ነዳጅን በበርሜል አጓጉዘው በችርቻሮ ለሚሸጡ ነጋዴዎች ፈቃድ በመስጠት ክፍተቱን ለመሙላት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

<<የነዳጅ ሀብት እንደ አገር በውድ በውጭ ምንዛሬ የሚገባ በመሆኑ የንግድ ሥርዓቱም ከፍተኛ ጥናትና ጥንቃቄ ይፈልጋል>> ያሉት ሔኖስ፣ የነዳጅ አዳዮች ማኅበር ላቀረበው የትርፍ ማሻሻያ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ጊዜ የወሰደውም ለዚህ ነው ይላሉ። ትርፉ ሊሻሻል የሚችልበትን መጠንና ማሻሻያው በትክክል የሚወጣበትን ቀን ግን መናገር አልችልም ብለዋል።

የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ኤፍሬም እንደሚሉት ከሆነ ማኅበሩ አንድ ብር ከ25 ሳንቲም በሊትር የትርፍ ጥያቄ ያቀረበው ከዓመት በፊት መሆኑና ጥያቄው ቶሎ ምላሽ ያልተሰጠበት በመሆኑ፣ ጥያቄው ከቀረበ በኋላ ያለው የዋጋ ንረት በብዙ ዕጥፍ መጨመሩን አንስተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here