ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)
ከሦስት ዓመት በፊት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ኃይሎች በአጋርነት አቋቁመነዋል ያሉት “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት” ሥራውን እየሰራ መሆኑን የሽግግር መንግሥቱ አባል ነን ያሉ አካላት አስታውቀዋል፡፡
በሽግግር መንግሥቱ እንቅስቀሰሴ ውስጥ ያሉ አካላት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተካሄደ ማግሥት በ2013 ላይ ተመስርቷል የተባለው የሽግግር መንግሥት ኮሚቴ ተዋቅሮ በይፋ ሥራውን እየሰራ ይገኛል፡፡
ኮሚቴው አሁን ላይ በርካታ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሥራዎቹ መካከል ወደፊት በኦሮሚያ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን ብቻ የተከተለ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት ማቋቋም፣ በኹሉም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል፣ በዋናት ደግሞ የዜጎችን ሰላም እና ድኅንነት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማቆም ነው ተብሏል፡፡
“አገሪቷ አሁን ላይ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል አንጻር ወደፊት አገር እንዳይፈርስ ወይም ሕዝቦች እንዳይበተኑ ይህ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት አገርን ከማሻገር አንጻር ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው፡፡” ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋረቻቸው የዚሁ እንቅስቃሴ አባል ጠቁመዋል፡፡
አባላቱ እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ውድቀት ከፍተኛ ግጭትን በመፍጠሩ እና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ አገሪቷን በማምራቱ፣ “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት” ለመመስረት እንደ ቁልፍ ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት” ምስረታን፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ)ን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጭምር የሃሳቡ ደጋፊ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የሽግግር መንግሥቱ እንቅስቃሴ ኮሚቴ አባላት ከኹለት ዓመታት በላይ በእስር ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፤ አሁን ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ ነጻ ተብለው ከእስር በመውጣት ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከሰሞኑ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፤ ሕዝቡ ጥቅም በመረዳት የዓላማው ደጋፊ እንዲሆንና ከሽግግር መንግሥቱ ጎን በመቆም አገርን ከመበተን እንዲያድን ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
ፓርቲዎቹ የሽግግር መንግሥት አቋቁመናል ያሉት፤ ኦነግና ኢፌኮ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ጊዜው አብቅቷል” በማለት ነበር፡፡ በወቅቱም የክልሉ መንግሥት የፓርቲዎቹን ሀሳብ በጥቅል ኮንኖት እንደነበርም ይታወቃል፡፡
ፓርቲዎቹ “ሕዝቡ የሚወክሉትን በሕግ እሰኪመርጥና የራሱን ቅቡል መንግሥት አስኪያቋቁም ድረስ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምለት ይፈልጋል” ብለው እንደነበርም ይታወሳል፡. በወቅቱ ኦነግና ኦፌኮ “አሁን ያለዉን የአገሪቱን ፖለቲካ በጥልቀት ካጤኑና ከመረመሩ በኋላ ከምሁራንና ከሰፊዉ ሕዝብ ጋር በመወያየት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት አቋቁመዋል” ሲሉ ባወጡት የሽግግር መንግሥት አዋጅ ላይ አስፍረው እንደነበርም ይታወቃል።



