በኦሮሚያ ክልል በ12 ዞኖች በተከሰተው የወባ በሽታ ከ500 ሺሕ በላይ ሰዎች መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ደረጀ አዱኛ፣ በሽታው እንደ ክልሉ በወረርሽኝ ደረጃ መኖሩን እና ከ500 ሺሕ ሰዎች በላይ መያዛቸውን መረጋገጡን ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
በተለይም ተፈናቃዮች በብዛት ባሉበት ምስራቅ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂ እንዲሁም ቄለም ወለጋ ዞኖች ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው፣ በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 19 ሺሕ 613 ነው ብለዋል።
በክልሉ አጠቃላይ የተፈናቃይ ቁጥር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተፈናቃዮችም በበሽታው መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
በበሽታው ከተያዙ በኋላ ወደ ህክምና ተቋመት ሲሄዱ አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ካሉ በኋላም፣ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አጎበር ለሕብረሰቡ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
ከ900 ሺሕ በላይ የሚሆኑት አጎበር ደግሞ የጸጥታ ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ ማድረስ አለመቻሉንም ጠቅሰው፣ በሆሮ ጉዱሩ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች የጸረ ወባ ኬሚካል መረጨቱን ገልጸዋል፡፡
ይህም ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የጸጥታ ችግሩ የአጎበር ስርጭት እና የጸረ ወባ ኬሚካል የመርጨት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን አመላክተዋል።
ሰዎች የበሽታውን ምልክት ሲያዩ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋማት አለመሄዳቸው ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
በአካባቢው ያሉ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማስወገድ እና ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ባለመፍጠር የበሽታውን ስርጭት መቀነስ እንደሚቻልም ነው የተጠቆመው።



