ኢሰመኮ በእስር ላይ በሚገኙ የኦነግ አመራሮች ዙሪያ ለመወያያት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ቀጠሮ መያዙን ገለጸ

0
335

አርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ በሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች ዙሪያ ለመወያያት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ቀጠሮ መያዙን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በዳሳ ለሜሳ፤ ኮሚሽኑ በእስር ላይ ስለሚገኙ የግንባሩ አመራር፣ አባላት እና ደጋፊዎችን ኹኔታ ሲከታተል እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አውስተዋል።

ኃላፊው አክለውም፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት እና ደጋፊዎች ከሕግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ በጅምላ ተይዘው በእስር ቤት እንደሚገኙ በመጠቆም፤ ኮሚሽኑ ባደረገው ብርቱ ክትትል ከእስር የተፈቱ ቢኖሩም፣ አሁንም ሰባት የሚሆኑ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች በማረሚያ ቤት ውስጥ ናቸው ብለዋል። ለዚህም እልባት ለመስጠት ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያወጣቸው መግለጫዎች እና በሚያዘጋጃቸው መድረኮች አመራሮቼ፣ አባላት እና ደጋፊዎቼ ከሕግ አጋባብ ውጭ በእስር ላይ ይገኛሉ በማለት በተደጋጋሚ ሲገልጸ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል፤ በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች እና በሕግ ታራሚዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሱ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጨምሮ ገልጿል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here