አርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)
በአገር አቀፍ ደረጃ የታለመለት የነዳጅ ደጎማ ስርዓት ተጠቃሚ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 177 ሽሕ ብቻ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ለአዲሰ ማለዳ ገልጿል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ፤ በዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓት ከተመዘገቡት 772 ሺሕ ተሽከርካሪዎች መካከል ተደጓሚ የሆኑት 177 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም “በኹሉም ክልሎች ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ 300 ሺሕ ተሽከርካሪዎች አሉ ቢባልም፤ እስካሁን በባለስልጣኑ ተመዝግበው ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ የሆኑት ግን 200 ሺሕ የማይሞሉ ናቸው።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከክልሎች የተላከው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ያመላክታል ነው ያሉት።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተሽከርካሪዎችን ቁጥር ማወቅ፤ ከውጭ የሚገባውን የነዳጅ መጠን ለመወሰን ያስችል እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ በየጊዜው እንደአገር የሚቀርበው የተሸከርካሪ ብዛት መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ገደማ ጠቅላላ የተሽከርካሪ ቁጥር ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ጠቅሰውም፤ “በመላ አገሪቱ ከሚያዚያ 16/2015 ጀመሮ ተግባራዊ በተደረገው ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓት የተመዘገበው የተሽከርካሪ ብዛት 772 ሺሕ መሆኑ ቁጥሩ በትክክል እየታወቀ አለመሆኑን ያመላክታል።” ሲሉ ነው የገለጹት።
ይህን ችግር ለመፍታት ከዲጂታል ግብይት ምዝገባው የተገኙ መረጃዎችን በመያዝ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለማጣራት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አክለውም፤ የታለመለት የድጎማ ስርዓትን በአግባቡ እየተጠቀሙ ባልሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የድጎማ ቅነሳ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህም ደጎማውን ወደ ጎን በመተው ሕብረተሰቡ ላይ ያልተገባ ጭማሪ እያደረጉ ባሉ አሽከርካሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በሊትር 28 ብር ድረስ ድጎማ ይደረግላቸው ከነበረው ላይ ወደ 19 ብር ዝቅ እንዲል መደረጉን አክለዋል፡፡
ደጎማው ላይ የተደረገው ቅነሳም ቅጣት እንደሆነና የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ምንም አይነት ጭማሪ እንዳልተደረገ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት አገሪቱ በነዳጅ ግዥ የሚመጣውን የዕዳ ጫና ለመቀነስ በሚል በተለይ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ሲያደርግ መቆዩቱ ይታወሳል።



