ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ የተጣሉ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ተባለ

0
652

ሰሞኑን አምስት ወጣቶች እጃቸው ወደኋላ ታስሮ እና ዓይናቸው ተሸፍኖ ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘዋወር ተስተውሏል፡፡

አዲስ ማለዳም ስለ ክስተቱ ባደረገቸው ማጣራት ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎችን ያነጋገረች ሲሆን፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰዎች ወጣቶቹ ላይ ድርጊቱ የተፈጸመው በምዕራብ ወለጋ ዞን ቂልጡ ካራ ከተማ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እጃቸው ወደ ኋላ ታስሮ እና ዓይናቸው ተሸፍኖ ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው የሚታዩት ወጣቶች ኢያሱ ካሳሁን፣ አበበ ዱፌራ፣ ደሳለኝ ቡልቻ፣ ተስፋዬ ተርፋሳ እንዲሁም ኦብሲ ዲነግዴ እንደሚባሉና የቂልጡ ካራ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።

ወጣቶቹን የመንግሥት የጸጥታ አካላት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራውና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት በእስር ቤት ካቆዩአቸው በኋላ ከማረሚያ ቤት በማውጣት ቂልጡ ካራ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ እንደወሰዷቸው ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት።

ወደ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ከተወሰዱ በኋላም ጉድጓድ ራሳቸው እንዲቆፍሩ ተደርጎ፣  እጃቸውን የኋሊት በማሰርና ዓይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን ከነሕይወታቸው ጉድጓዱ ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች መከተታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከፍተኛ ድብደባ እና የሰብአዊ መብጥ ጥሰት የደረሰባቸው በመሆኑም፣ ከአምስቱ ወጣቶች አንደኛው በደረሰበት ጉዳት ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ወጣቱ ለአራት ቀናት ሕክምናውን ተከታትሎ ወደ ቤተሰቡ ከተመለሰ በኋላም፣ በድጋሜ ወደ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዲመለስ መደረጉ ነው የጠቆሙት።

ወጣቶቹ ጉድጓድ ውስጥ ከተጣሉበት ቀን ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዝናብ እና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው ነበር የተባለ ሲሆን፣ አሁን ላይ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ተጠቅሳል።

የወጣቶቹ ቤተሰቦች ምግብ እና ሌሎች ቁሳቆሶችን ይዘው ቢሄዱም፣ መገናኘት የማይፈቀድላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው ተብሏል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከአካባቢው የመንግሥት ሹመኞችና ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here