የሕወሓት ኃይሎች ጠለምት በመግባታቸው ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ተገለጸ

0
1165

በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የሕወሓት ታጣቂዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጀበው በምዕራብ ጠለምት ወረዳ ሲንቀሳቀሱ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር የጠለምት አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ ጸጋየ እሸቴ ‹‹ትጥቅ ያልፈቱና በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ የሕወሓት ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት ታጀበው ወደ ጠለምት እየገቡ ነው›› ብለዋል፡፡

በዚህም ሐምሌ 02/2015 ረፋድ ላይ በሕወሓት ታጣቂዎችና በአካባቢው በሚገኙ የፋኖ፣ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት መካከል ለ30 ደቂቃ ገደማ የቆየ ተኩስ ለውውጥ መደረጉን ተናግረዋል።

አክለውም ‹‹ታጣቂዎቹ በጠለመት ተከዜ ዙሪያ አዲስ ጦርነት ለመጀመር ልዩ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ በመከላከያ ሠራዊት ታጅበውም ጠለምት ገብተው ይወጣሉ›› ሲሉ ተደምጠዋል።

<<ከአንድ ሳምንት በፊት የሕወሓት አመራሮች በሽሬ ከተማ ጠለምትንና ራያን በአጭር ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል ለማካተት ሲመካከሩ ነበር>> ያሉት ጸጋዬ፣ ከእሁድ ሐመሌ 02/2015 ጀምሮ የሕወሓት ታጣቂዎች በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው እስናይፐር እና ዲሽቃ የታጠቁ የሕወሓት ኃይሎች በስፋት ሲገቡ ነበር ብለዋል።

በዚህም የሕወሓት ታጣቂዎች በስምንት መኪና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅበው ሲገቡ በአካባቢው ካሉ የፋኖ፣ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት ጋር ዲማ እና ፍየል ውሃ በተባሉ ቦታዎች  ላይ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተገልጿል።

ትጥቅ ያልፈቱ የሕወሓት ታጣቂዎችን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ስንቅ እና ትጥቅ እያቀበሏቸው መሆኑና፣  በጦር መሳሪያ አጅበው ወደ ጠለምት እንዲገቡ እገዛ ማድረጋቸው ሕዝቡን አስቆጥቷል ነው የተባለው።

በጠለምት ሶስት ቀበሌዎች እስካሁን ከሕወሓት ኃይሎች ነጻ አለመውጣታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ጠለምትን እና ራያን እንዲሁም ወልቃይትን ለመቆጣጠርም ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም በጠለምትና አካባቢው ሰሞኑን ውጥረት መንገሱ ነው የተጠቆመው።

የአላማጣ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ እያሱ በበኩላቸው የሕወሓት ኃይሎች በአካባቢው ሁከት ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ነው ሲሉ ገልጸው፣ በራያ እና አላማጣ አቅራቢያ ሕወሓት በርካታ የታጠቀ ኃይሉን እያስጠጋ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለኹለት ዓመት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገ የሰላም ስምምነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ሆኖም ይህን ስምምነት ወደ ጎን በመተው ታጣቂዎቹ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን እየፈጸሙ ይገኛሉ የሚል አቤቱታዎች ይቀርባሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here