በኦሮሚያ ክልል ከምስራቅ ቦረና ዞን አዲስ አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ዳግም ማገርሸቱን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።
ነዋሪዎቹ ከአዲሱ የምስራቅ ቦረና ዞን አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በአባገዳዎች፣ በሐይማኖት አባቶች እና በክልሉ መንግሥት ጥረት ተፈቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም ካለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 04/2015 ጀምሮ ችግሩ ዳግም ማገርሸቱን ገልጸዋል።
በዚህም ሰኞ ሐምሌ 03/2015 ሌሊት በጎሮ ዶላ ወረዳ ልዩ ሥሙ ኪሊዌ በተባለ አካባቢ “ቄሮ” በማለት ራሳቸው የሚጠሩ አካላት ከነጌሌ ቦረና የሚመጣ የግለሰብ የጭነት መኪና እና አንድ የሕዝብ ማመለሻ አውቶቡስ ማቃጠላቸውን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡
በአካባቢው አሁንም ድረስ ከፍተኛ ውጥረት በመኖሩ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በየጊዜው በሚደረጉ መሰል ድርጊቶችም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ ተጠቁሟል።
በተለይም ከነገሌ ቦረና ከተማ ወደ ጎሮዶላ በሚወስደው መንገድ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር በመኖሩ በአካባቢው ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ነው የተጠቀሰው፡፡
በአካባቢው በተለይም ረቡዕ ሐምሌ 5/2015 ሙሉ ቀን ውጥረት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ሥፍራው ለመግባት ሙከራ ቢያደርግም ነዋሪዎቹ መንገድ በመዝጋት አላስገባም ማለታቸው ተነግሯል።
ሆኖም በትናንትናው ዕለት የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው መግባቱን ተከትሎ፤ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩ ተጠቁሟል።
የምስራቅ ቦረና ዞን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ መሳይ ጥላሁን ሰሞኑን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከአንድ ወር በፊት በአባገዳዎች፣ በኃይማኖት አባቶች እና በክልሉ መንግሥት ጥረት ተፈትቶ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ዳግም ግጭትና አለመግባባት መፈጠሩን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
“አሁን ላይ ሕዝቡ ለምን ዳግም ወደ ተቃውሞ እንደተመለሰ ብዙም ግልጽ የሆነ ነገር የለም።” ያሉት ኃላፊው፤ ጉዳዩን ለማጣራትና ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አክለውም በአካባቢው የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር በቀጥታ ከዞኑ አዲስ ከአደረጃጀት ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን በማንሳት፤ በአካባቢው የተጣቁ ኃይሎች በስፋት ስለሚንቀሳቀሱ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ውድመት እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡
በሕዝቡ በኩል የክልሉ መንግሥት ማህበረሰቡን በበቂ ሁኔታ ሳያወያይ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው የሚለው ቅሬታ ተገቢ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ነገር ግን እንደ ዞን የሚመለከታቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ ጠርተን አወያይተናል ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ ቀደምም የአካባቢው ማህብረሰብ የክልሉ መንግሥት ያሳለፈውን አዲስ የአደረጃጀት ውሳኔ በመቃወም መንገድ በመዝጋት ጭምር ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
የክልሉ መንግሥት የካቲት 27/2015 ምስራቅ ቦረና የተሰኘ አዲስ ዞን መመስረቱን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያቀርበው የጎሮዶላ ወረዳ ከጉጂ ዞን ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን በመካለሉ እንደሆነ ይጠቀሳል።



