በትግራይ ክልል የሚገኘው የአክሱም ሐውልት አስቸኳይ ጥገና ካልተደረገለት ሊወድቅ ይችላል ሲል የአክሱም ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የአክሱም ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገብረመድኅን ፍፁምብርሃን ሐውልቶቹን የተሸከመዉ ጥንታዊ የመቃብር ሥፍራ በክረምት ዉሃ እና ሌሎች ምክንያቶች መፈራረሱን ጠቅሰው፤ ከጦርነቱ በፊት ከጣልያን በመጡ ባለሙያዎች ጥናት ተደርጎ በጣሊያን መንግሥት ዕድሳት ይደረግለታል ተብሎ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የጥገና ሥራውን ይሰራል የተባለው ቡድን ከዚያ በኋላ ወደ ሥፍራው እንዳልተመለሰ ገልጸዋል።
በአክሱም ከተማ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተሰሩ በርካታ ሐውልቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከእነዚህ መካከል በመጠኑ ትልቅ የሆነው እና ቁጥር ሦስት ተብሎ የሚታወቀው ሐውልት በብረት ምሶሶዎች ተደግፎ ተንጋዶ እንደሚታይ ነው የጠቆሙት።
ስለሆነም ሐውልቱ አስቸኳይ ጥገና እና ዕድሳት ካልተደረገለት ሊወድቅ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ሐውልቶቹን ተሸከሞ ያለው “ሞዘልየም” የተሰኘው ጥንታዊ መቃብር በጊዜያዊነት ለመጠገን የፌዴራል መንግሥት ከሳምንት በፊት መጠነኛ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ “ሆኖም ግን ቅርሱን ለመታደግ ይህ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተጨማሪም በዓመት እስከ 25 ሺሕ የሚገመቱ የውጭ አገር ቱሪስቶች ይጎበኙት ነበር የተባለው ከአክሱም ሐወልቶች አቅራቢያ የሚገኝ ሙዚየም፤ በጦርነቱ ወቅት በደረሰበት ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት እስካሁን ምንም ዓይነት ጥገና እንዳልተደረገለት አብራርተዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የአክሱም አውሮፕላን ማረፍያ እንዲሁ እስካሁን እድሳት እንዳልተደረገለት እና ወደ አገልገሎት እንዳልተመለሰ ገልጸዋል፡፡
የአክሱም ከተማ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ገቢ የምታገኘው ከቱሪዝሙ ዘርፍ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ አካባቢው ሰላም ቢሆንም ወደ ከተማዋ የሚመጣ ጎብኚ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በዋናነት የሐወልቶቹ አስተዳደርና ጥገና ጉዳይ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ልዑካኑን ወደ አክሱም ከተማ በመላክ የሐውልቶችን ሁኔታ መመልከቱንና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የሚላክ የጥናት ውጤት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም ሐውልቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመጠገን ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፌደራል መንግሥቱ ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥቶ ሊከታተለው እና ቅርሱን ሊታደገው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡



