አስራ ሦስት ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል ኔትዎርክ ይዘረጋል ተባለ

0
560

አርብ ሐምሌ 21 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት አስራ ሦስት ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል ኔትዎርክ ይዘረጋል ሲል ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻም ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የ2016  ዕቅድ አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ የተያዘው ዕቅድ፣ ተቋሙ ቀድሞ የነበረውን 78 ሚሊዮን ደንበኛ ወደ 92 ሚሊዮን ማድረስ ይስችላል ያሉ ሲሆን፤ በዚህም በቀጣይ ዓመት 8 ነጥብ 3 በመቶ  የደንበኛ ዕድገት ይመዘገባል ብለዋል።

እንዲሁም 998 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች (ታወር) ይገነባሉ ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ እነዚህም በ140 የገጠር ከተሞች የሚገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራቸው ክንውኖች መካከል የፋይበር ዝርጋታ አንዱ መሆኑን በመጥቀስም፤ በ2016 1 ሺሕ 376 ኪሎ ሜትር ፋይበር እንደሚዘረጋና እንደአገር ያለውን የፋይበር ዝርጋታ መጠን ወደ 24 ሺሕ 552 ከፍ እንደሚያርገው ጠቁመዋል፡፡

አክለውም፤ በቴሌ ብር አገልግሎት በኩል ባለፈው ዓመት ከነበረው 34 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደንበኛ በቀጣይ ዓመት ወደ 44 ነጥብ 1 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ መታሰቡን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የ4G አድቫንስ፣ 5G እና 3G የኔትወርክ አገልግሎትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ እንዲሁም ሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ24 በመቶ ለመጨመር ማቀዱንም ነው የገለጹት።

በጦርነት እና በተለያዩ አደጋዎች የወደሙ የተቋሙን ንብረቶች ጠግኖ ወደ ሥራ ማስገባትም ሌላው የ2016 ዕቅዳችን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ እንደአገር የተያዘውን የዲጂታል ገበያ ስርዓት ለመደገፍም በቀጣይ ዓመትም በትምህርት፣ በጤና፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በግብርና፣ በቱሪዝም በትራንስፖርት፣በኮንስትራክሽን እንዱሁም በመዝናኛው ዘርፍ ያለውን ግብይት ቀልጣፋ በሆነ ዲጂታል ስርዓት ለመከውን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።

ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 75 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣዩ የበጀት ዓመት 90 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማሰብሰብ ማቀዱም ተነግራል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here