ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር በዋናነት በመተማ በኩል የሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሕገወጥ ንግድ መባባሱ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጭምር ተሳታፊ መሆናቸውን የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ተቋም ሠራተኛ “የሱዳን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ከጎንደር እና አካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን የሚደረገው የንግድ ዝውውር ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጸጥታ አካላት ተባባሪ እየሆኑ ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በመተማ ከተማ እና በሱዳን ድንበር አካባቢዎች ቡናን ጨምሮ ሳሙና፣ ብስኩት፣ የታሸገ ውሃ፣ ሻይ ቅጠል እንዲሁም ሌሎች ሸቀጣሸቀጦች በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ሱዳን እየተጓጓዙ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ወደ ሱዳን በሕገወጥ መንገድ የሚወጡ እቃዎችን መጨመሩን ተከትሎም፤ በጎንደር ከተማ እና አካባቢው የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችና ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን አዲስ ማለዳ ከከተማዋ ነዋሪዎች ተገንዝባለች።
ለአብነትም እስከቅርብ ጊዜ 25 ብር ሲሸጥ የነበረ የልብስ ሳሙና ወደ 78 ብር ከፍ ማለቱን እና የሻይ ቅጠል ከ25 ብር ወደ 52 ብር ማደጉን መረዳት ተችሏል።
በጸጥታ አካላት የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር አናሳ መሆን እንዲሁም የጸጥታ አካላት ራሳቸው ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ጉቦ በመቀበል ተባባሪ መሆናቸው ሕገወጥ ንግዱን አባብሶታል ነው የተባለው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ የግጭትና የኃይማኖት ዕምነት ጉዳዮች የሥራ ሂደት ኃላፊ ዮናስ ጋዲሳ፤ ባለሃብቶች በንግድ ፈቃድ አማካኝነት ከተለያዩ ቦታዎች ገዝተው የሚያመጡትን ዕቃ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን እያስወጡ መሆኑን ተከትሎ ሕገወጥ ንግዱ ተባብሷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አክለውም ዘይት፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ቡና እና የሻይ ቅጠልን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ሱዳን በስፋት እንደሚወጡ ጠቁመው፤ ሱዳን ድንበር አካባቢ ለሚገኙ የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት ለአንዳንዶቹ “ለሻይ” በሚል ብር በመስጠት የሚያስወጡ መኖራቸውን እንሰማለን ሲሉ ተደምጠዋል።
ከሕገወጥ ንግዱ በተጨማሪ ግጭቱን ተከትሎ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎችን ጉቦ የሚቀበሉ የተወሰኑ የጸጥታ አካላት፤ ኬላ ላይ ሳይፈተሹ እንዲያልፉና በጸጥታ አካላት ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገቡ የሚያደርጉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።



