ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጻግብጅ ወረዳ በሕወሓት እና አገው ሸንጎ ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ምንነቱ ባልታወቀ ወረርሽኝ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን የጻግብጅ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የጻግብጅ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መኳንንት ጣምተው፤ የወረርሽኙ ምልክት ከሐምሌ 22/2015 ጀምሮ መታየቱን ገልጸው፤ ማክሰኞ ዕለት ብቻ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡
የበሽታው ምልክቶቹ ትኩሳት፣ ወደላይና ወደታች ማለት፣ ማሳከክ፣ ቅዠት፣ ሳል እና ተቅማጥ አዘል አጣዳፊ በሽታ ናቸውም ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም ወረርሽኙ የተከሰተው የሕወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረው በያዟቸው ሠላምየ፣ ሽሚላ፣ ጨረየ እንዲሁም በድ ተብለው በሚጠሩ አራት ቀበሌዎች መሆኑንም ነው የገለጹት።
በወረዳው የጤና ተቋማት በጦርነቱ ወቅት መውደማቸውን ተከትሎም አገልገሎት እየሰጡ አለመሆኑን ገልጸው፤ “በወረርሽኙ ለተያዙ ሰዎች ጊዜያዊ የሕክምና እርዳታ ለማደረግ ቢሞከርም አካባቢው በሕወሓት ኃይሎች ሥር በመሆኑ ማንኛውም የመንግሥት የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ወደ አካባቢው እንዳይገቡ አድርጓቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በመሆኑም መንግሥት በአስቸኳይ ወደ አካባቢው የጤና ባለሙያዎችን ልኮ ሕክምና መስጠት ካልተቻለ ወረርሽኙ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት አካባቢው በሕወሓት እና አገው ሸንጎ ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ገብተው ሕክምና መስጠት አይችሉም ያለው የወረዳው ጽህፈት ቤት፤ ገለልተኛ አካል ገብቶ በሽታው እንዲጠናና የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለሚመለከተው አካል ጥሪውን አቅርቧል።



