ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከመጭው አርብ ሐምሌ 28/2015 ጀምሮ መደበኛ ጉባኤውን የሚያካሂደው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፤ በቅርቡ በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ 12ኛ ክልል ሆኖ ከተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ እንደሚያደርግ አዲስ ማለዳ ከምክር ቤት አባላት ሰምታለች።
ምክር ቤቱ አርብ እና ቅዳሜ ለኹለት ቀናት በሐዋሳ ከተማ ለሚያደርገው መደበኛ ጉባኤ፤ የምክር ቤት አባላቱ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ሐዋሳ ገብተው እንደሚያደሩና ጉባኤውን ለማካሄድ ሙሉ ዝግጅት መደረጉ ተጠቁሟል።
እንዲሁም ሀድያ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ፣ አላባ፣ ከንባታ እና የም የተሰኙ አምስት ዞኖችን እና አንድ ልዩ ወረዳን ይዞ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተባለውን ክልል መመስርት የምክር ቤቱ ሌላኛው አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አባላቱ ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 28/2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የጌዴኦ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶና አሌ ልዩ ወረዳዎች “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል ስያሜ 12ኛ ክልል በመሆን ምክር ቤቱን በአባልነት መቀላልቀሉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተነጥለው ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሲሆን፤ በቀጣይም አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳን የያዘው ክልል በይፋ ከተዋቀረ በኋላ ነባሩ የደቡብ ክልል የሚያከትም ይሆናል።



