በራያና ጠለምት ጉዳይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ሀሳብ በመቅረቡ የጠለምት ተወካዮች ስብሰባ ረግጠው ወጡ

0
1709

ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ክልል መንግሥት ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 22/2015 በባህር ዳር ከተማ በተደረገ ስብሰባ ላይ በራያ እና ጠለምት አካባቢዎች የሚነሳው የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እልባት እንዲያገኝ ሀሳብ ማቅረቡን ተከትሎ፤ ሀሳቡን አንቀበልም ያሉ የጠለምት ተወካዮች ስብሰባውን ረግጥው መውጣታቸውን አዲስ ማለዳ ከተሳታፊዎች አረጋግጣለች።

ስብሰባውን ረግጠው የወጡት የጠለምት አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት፤ “በስብሰባው ላይ “በጠለምት ሕዝበ ወሳኔ ይካሄዳል” እንዲሁም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት “ጠለምት እና አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ይተዳደራል” የሚል ሀሳብ በመቅረቡ ስብሰባውን ረግጠን ለመውጣት ተገደናል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንዲሁም በጠለምት እና አካባቢው የወረዳና የቀበሌ የመንግሥት መዋቅር እንዲፈርስና በአዲስ መልኩ በፌደራል መንግሥቱ አስመራጭነት አዲስ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች እንዲመረጡ ሀሳብ መቅረቡን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከጠለምት የተፈናቀለ የትግራይ ክልል ነዋሪ አለመኖሩ እየታወቀ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ወደ ጠለምት ይመለሳሉ የሚል ሀሳብ ስብሰባው ላይ መቅረቡን አንስተው፤ ይህም “በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በተፈናቃይ ሥም ወደ ቦታው በማስገባት የጠለምት ሕዝብ የማይቀበለውን ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ የታሰበ ነው” ብለዋል።

አባላቱ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግሥት አመራሮች ከዚህ የስብሰባ ቀን ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በባህር ዳር ውይይት አካሂደዋል።

የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ ሃይሉ አበራ በበኩላቸው፤ በባህርዳር በተደረገው ስብሰባ የራያ አላማጣ አካባቢዎች ጉዳይ በሕዝበ ወሳኔ መሠረት እንዲፈታ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“የራያ አላማጣ እና አካባቢው ሕዝብ የማንነት ጥያቄው በሕዝበ ወሳኔ መሰረት እንዲፈታ ከወራት በፊት በፊርማው ያረጋገጠ በመሆኑ፤ በስብሰባው የቀረበውን ሀሳብ ተቀብለን ሕዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም ዝግጅት ላይ ነን፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሕዝበ ወሳኔ እንዲካሄደም ከ150 ሺሕ በላይ የአካባቢው ሕዝብ የፈረመበት ደብዳቤ ለፌድሬሽን ምክር ቤት መግባቱን አውስተዋል፡፡

በአንጻሩ ከወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች በስብሰባው ላይ የተሳተፈ አካል አለመኖሩ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች በሕዝበ ውሳኔ ሊፈቱ እንደሚችሉ ጥቆማ መስጠታቸው ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here