በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የነበረው የአስራ ኹለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መቋረጡ ተሰማ

በዩንቨርስቲው አቅራቢያ በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ ፈታኝ መምህር እና ሦስት ተማሪዎች መገደላቸው ተገልጿል

0
1393

አርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በ“ፋኖ” ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለውን ውጊያ ተከትሎ፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ የሚገኘው የአስራ ኹለተኛ ክፍል የመልቀቅያ ፈተና መቋረጡን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ከሐምሌ 25/2015 ጀምሮ ለአራት ቀናት በአገሪቷ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት መሰጠት የጀመረው የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መልቀቅያ ፈተና፤ በጎንደር ከተማ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና የ“ፋኖ” ታጣቂዎች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ውጊያ ተከትሎ በዩንቨርሲቲው ሲሰጥ የነበረው ፈተና በትናንትናው ዕለት መቋረጡን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህም ፈተና ላይ የነበሩ ተማሪዎች በተኩስ ልውውጡ ተደናግጠው ፈተና አቋርጠው መውጣታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ተማሪዎች ጠዋት ላይ የተሰጠውን ፈተና ተፈትነው የከሰዓቱን አቋርጠው መውጣታቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአንጻሩ ሌላ አንድ የከተማ ነዋሪ በዩንቨርሲቲው ትናንት ሊሰጥ የነበረው ፈተና ሙሉ ለሙሉ እንዳልተሰጠ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በዛሬው ዕለት መምህራን እና ተማሪዎች ዩንቨርስቲውን ለቀው መውጣታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ትናንት በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ ፈታኝ መምህር እና ሦስት ተማሪዎች መገደላቸውን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ሰምታለች፡፡

የመከላከያ ሠራዊት በትናንትናው ዕለት በዩኒቨርሲቲው ማራኪ፣ ቴዎድሮስ እንዲሁም ፋሲል ካምፓሶች በሚገኙ ተራራማ ቦታዎች ውስጥ ከባድ የጦር መሳሪያ አጥምዶ እንደነበርም ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በተደጋጋሚ የደወለች እና መልዕክት ያስቀመጠች ቢሆንም፤ ባለመመለሳቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መርኃ ግብር መሰረት የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከሐምሌ 19 እስከ 21/2015 ባሉት ቀናት የመልቀቂያ ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ደግሞ ከሐምሌ 25 እስከ 28/2015 ፈተናውን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here