ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሐዋሳ ከተማ ከሐምሌ 28/2015 ጀምሮ ለተከታታይ ኹለት ቀናት ሲካሄድ የነበረውን የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ፣ ለሦሰተኛ ቀን ማለትም ሐምሌ 30/2015 እንዲቀጥል ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፤ ጉባኤው ባልታወቀ ምክንያት እንዲሰረዝ መደረጉን አዲስ ማለዳ ከምክር ቤት አባላት ሰምታለች፡፡
ምክር ቤቱ ለኹለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ በኹሉም አጀንዳዎች ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ ጉባኤው ለሦስተኛ ቀን እንደሚቀጥል ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ቅዳሜ ሐምሌ 29/2015 ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በስልክ ቁጥር አድራሻቸው “ለሦሰተኛ ቀን ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ጉባኤ ተሰርዟል” የሚል መልዕክት ከምክር ቤቱ አፈጉባኤ እንደደረሳቸው አባላቱ ተናግረዋል፡፡
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምክር ቤት አባል “መደበኛ ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት በጉባኤው ወይይት ይካሄድባቸዋል የተባሉትን አጀንዳዎች አጠናቀናል። ለሦስተኛ ቀን የተቀጠረው ጉባኤ ግን በምን ጉዳይ እንደነበር የተገለጸልን ነገር አልነበረም፡፡” ብለዋል፡፡
ለኹለት ቀናት በተደረገው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ፣ 12ኛ ክልል ሆኖ ለተዋቀረው አዲስ ክልል ስልጣን ከማስረከብ ውጭ፤ የክልሉ ዋና መቀመጫ እንዲሁም የክልሉ የመንግሥት ተቋማት መቀመጫ ዙሪያ የተወራ ነገር አለመኖሩ ነው የተገለጸው።
ሆኖም ለሦስተኛ ቀን ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ጉባኤ፣ ለአዲሱ “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ዋና መቀመጫ ከተማን የመሰየም እንዲሁም፤ የክልሉ መንግሥት ቢሮዎችን መቀመጫ በተመለከተ ሊሆን እንደሚችል የምክር ቤት አባላቱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በመሆኑም ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ ከተማ ስያሜ እና የመንግሥት ተቋማት መቀመጫ ክፍፍል ጉዳይ ላይ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱን ተከትሎ፤ በጉዳዩ ላይ ውይይት ቢደረግ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ለሦስተኛ ቀን የታቀደው ጉባኤ ሳይዘረዝ እንዳልቀረም ተጠቁሟል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘም በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች እሁድ ሐምሌ 30/2015 የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ታውቋል።
አርባ ምንጭ ከተማ አዲስ የተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የርዕሰ መስተዳደር ቢሮ፤ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና መቀመጫ ትሆናለች ሲባል የቆየ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ እንዲዞር መደረጉን ከክልሉ ባለስልጣናት መረጃ ደርሶናል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ሐምሌ 28 እና 29/2015 ባካሄደው ጉባኤ፣ በቅርቡ በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ 12ኛ ክልል ሆኖ ከተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጋር የስልጣን እርክክብ አድርጎ ጉባኤውን አጠናቋል።



