በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በዓመት 300 ሺሕ ሰዎች እንደሚሞቱ ተገለጸ

አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ማለትም በልብ ህመም፣ ካንሰር፣ ደም ግፊትና ስኳር በሽታዎች በዓመት 300 ሺሕ ያህል ሰዎች እንደሚሞቱ የጤና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እና የአእምሮ ጤና ዘርፍ ተወካይ ኃላፊ አዲሱ ወርቁ፤ “እንደ ስኳር፣ ደም ግፊትና ካንሰር በመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአካባቢ ለውጥ፣ አኗኗር እና አመጋገብ ለእነዚህ በሽታዎች አጋላጭ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ “በሽታዎቹ በቶሎ ምልክት ስለማያሳዩ ብዙ ሰው በሽታውን የሚያውቀው ከተያዘ አምስት እና 10 ዓመታት በኋላ ነው፡፡” ብለዋል። አስቀድሞ የጤና ምርመራ አለማድረግ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል ሲሉም አስረድተዋል።

የማህጸን ጫፍ እና የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ በስፋት እየታዩ መሆኑን ገልጸውም፤ ከሕመም በፊት አለመመርመርና በሽታውን ለመከላከል የተዘጋጁ ክትባቶችን አለመውሰድ በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ቀድሞ በእድሜ መግፋትና በዘር የሚመጣ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ሀያዎቹ መጨረሻ እና ሰላሳዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሰዎች ላይም በስፋት እየተስተዋለ ነው ብለዋል።

ይህም ለልብ፣ ስትሮክ እና ኩላሊት በሽታ የበለጠ አጋላጭ  ነው ያሉት ኃላፊው፤ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብ በሽታዎች እንዲስፋፉ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ፣ ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠን፣ ጨው እና ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግም ሌሎች ለበሽታዎች የሚዳርጉ መንስኤዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here