የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ግንባታ ማማከር ሠራተኞች ወቅቱን ያላገናዘበና እጅግ አነስተኛ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው ገለጹ

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ዲዛይን ግንባታ ማማከር የልማት ድርጅት ዉስጥ የሚሰሩ ከ200 በላይ ቋሚ ሠራተኞች ወቅቱን ያላገናዘበ እጅግ አነስተኛ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መስሪያ ቤቱ በ2009 በአዲስ መልክ ከተዋቀረ እና ሠራተኞቹ ድልድል ከተደረግላቸው በኋላ፤ ደመወዛቸው ቀድሞ በነበሩበት መስሪያ ቤት ይከፈላቸው በነበረው እንደሚቀጥል እንደተነገራቸው አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የድርጅቱ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“ሆኖም ለያዝነው ደረጃ ፈጽሞ ተገቢ ያልሆነ ደሞዝ ነው እየተከፈለን ያለው፡፡” ያሉት ሠራተኛው፤ በተመሳሳይ የሥራ ደረጃ የተለያየ ደሞዝ የሚከፈልበት ስርዓት መኖሩን አመላክተዋል።

“ቅሬታችንን በተደጋጋሚ ከሥራ አስኪያጅ እስከ ተጠሪ መስሪያ ቤቱ ድረስ ያቀረብንና እንዲስተካከልን የጠየቅን ቢሆንም እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሄ አላገኘንም፡፡” ሲሉም ገልጸዋል።

ተቋሙ ለሠራተኞቹ ደሞዝ የሚከፍልበት ስኬል የለውም ካሉ በኋላም፤ ዋናው ጥያቄያችን የደሞዝ ስኬል ቢሆንም፣ ተቋሙ ጥያቄያችንን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም ነው ያሉት።

ለሰራተኞቹ የተሰጣቸው የቅጥር ደብዳቤ የደሞዝ መጠንን የሚገልጽ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
ሌላኛው የድርጅቱ ሠራተኛ “ከ2009 ጀምሮ ሦስት ጊዜ መዋቅር ቢሰራም፤ ያለምንም የደሞዝ ስኬል ከምንሰራው ሥራ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ክፍያ ነው የሚከፈለን፡፡” ብለዋል።

እንዲሁም “እንኳን የመንግሥት መስሪያ ቤት ቀርቶ ሌሎች ትንንሽ ተቋማት የደሞዝ ስኬል አላቸው። ይሄ ሕገ ወጥ ተግባር ሠራተኛውን እየበደለ ነው፡፡” ሲሉ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።

አክለውም፤ “የሚከፈለን ደሞዝ ኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ እና ጥቅማጥቅም ባለመኖሩ በደል እየደረሰብን በመሆኑ፤ ጥያቄያችን በምክክር እንዲመለስ ባለፉት ሦስት ዓመት ጥረት ቢደረግም ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡” ብለዋል።

የሠራተኞቹ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ዲፕሎማ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ከአስር ዓመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ የሚከፈላቸው የወቅቱን የኑሮ ወድነት ያላገናዘብ ደሞዝ በአማካኝ ከ1 ሺሕ እስከ 2 ሺሕ 900 ብር መሆኑን ነው የተናገሩት።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር መስከረም ክንፈ ገብርኤል “የሠራተኞች ጥያቄ አግባብነት አለው፡፡” ሲሉ ገልጸው፤ አዲሱ መዋቅር በቅርቡ የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር የራሱ ሂደት እና የአሰራር ስርዓት ያለው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንዲሁም በከተማው ዉስጥ የተለያዩ በርካታ አጀንዳዎች መኖራቸውን በማንሳት፣ በድርጅቱ በኩል ጥናት ተደርጎ መግባቱን እና የማጽደቁ ሥራ የቦርዱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከደመወዝ ስኬሉ በተጨማሪ ዉስጥ ደንብም አብሮ የሚጸድቅ መሆኑንና እንደጸደቀ ወደ ሥራ የሚገባበት ሂደት መኖሩንም ነው የጠቆሙት።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here