ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዚህ በፊት በማይታወቁ የወባ በሽታ አምጭ ትንኞች የሚከሰት የወባ በሽታ እየጨመረ መምጣቱን፤ በፓን አፍሪካን የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያ ማህበር የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
“የወባ በሽታ ባለፉት ዓመታት የወባ ስርጭት መጠኑ ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፤ ባለፉት ኹለት ዓመታት ዉስጥ ግን በወረርሽኝ ደረጃ በመላው አገሪቱ ተዳርሷል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለውም፤ የወባ በሽታ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ያልነበሩ እና ጠፍተው የነበሩ ትንኝ ወለድ በሽታዎች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
“ለአብነትም ደንጊ የተባለው በሽታ በስፋት በእስያ አካባቢ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የበሽታ ታሪክ በፈረንጆች 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ ታይቷል፡፡” ካሉ በኋላ፤ በሽታው አድማሱን አስፍቶ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መታየቱን ጠቁመዋል።
“በሽታው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ባህሪውን፣ መከላከያ መንገዱ እና የምርመራ ሂደቱ አለመታወቁ ትልቅ የኅብረተሰብ የጤና ችግር ሆኖ መጥቷል፡፡” ነው ያሉት።
እንዲሁም ቅልጥም ሰባሪ እና የቢጫ ወባ በሽታ የሚባሉት በሽታዎች ቀድሞም ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩ ቢሆንም፤ የስርጭት መጠናቸው በጣም አነስተኛ የነበረ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ በርካታ ክፍሎች ላይ መታየት ጀምሯል ሲሉ ተደምጠዋል።
ለአብነትም በደቡብ ምዕራብ እስያ በስፋት የምትታወቀዋ አኔፌነስ ቴፈንሲ የተባለችው በሽታ አምጭ ትንኝ፤ ቀድም ብሎ በጅቡቲ በመከሰት ከሰባት ዓመት በፊት ደግሞ የበሽታው ምልክት በኢትዮጵያ መታየቱን አመላክተዋል።
ይህም ለመጀመሪያ የታየው በሶማሌ ክልል መሆኑን ጠቁመው፤ በመቀጠል በድሬድዋ፣ አፋር፣ መተሃራ፣ አዳማ፣ ወሎ፣ መተማ እንዲሁም በቅርቡ ጎጃም እና ቤኒሻንጉል አካባቢዎች የወባ ስርጭቱ መስፋፋቱን ገልጸዋል።
ይኸው የወባ በሽታ በተመሳሳይም፤ ኬኒያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን መዛመቱን እና ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገሮችም መስፋፋቱን ነው የጠቀሱት።
በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች በሽታውን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመቀነስ የሚሰሩ ሥራዎችን በማደናቀፍ የራሱ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል።
እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ለወባ በሽታ መስፋፋት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።
የፓን አፍሪካ የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያ ማህበር (PAMCA) ዘጠነኛው ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ሲሆን፤ ከመላው አለም ከ800 በላይ የሆኑ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች የተሳተፉበት ነው።
ይህ ጉባኤም አገር ዉስጥ ያሉትን ባለሙያዎች ከሌሎች አገራት ባለሙያዎች ጋር ትስስር የመፍጠርና ልምድ የመለዋወጥ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገራትና በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለጥናትና ምርምር ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውል የማድረግና ምክረ ሃሳብ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፓን አፍሪካ ወባ ትንኞች መቆጣጠሪያ ማኅበር በኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አቅዶ እየሠራ ሲሆን፤ ከጤና ሚኒስትር ጋር በመተባር በመሥራት ወደፊት የወባንና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ለመቆጣጠርና ለማስወገድ በጋራ መሥራትና እቅዱን ይፋ የማድረግ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ አክለውም፤ “በአገር ደረጃ ችግር ላይ ነው ያለነው በበሽታው ከሚያዘውና ከሚሞተው እንዳለ ሆኖ በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡” ሲሉ አሳስበዋል
ከኢትዮጵያ አንድ ሚሊየን ስኩዌር ስፋት ዉስጥ 75 በመቶ የሚሆነው ቦታ ለወባ በሽታ የተጋለጡ መሆኑ እና ከዚህም ውስጥ 69 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍልም ተጋላጭ መሆኑ ማህበሩ አመላክቷል።



