ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አሁን ላይ እተፈጸሙ ላሉ የጅምላ ግድያዎች እና አስከፊ ወንጀሎች “አገሪቷን እየመራሁ ነው” የሚለው መንግሥት ከተጠያቂነት አያመልጥም ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
“አገሪቷን እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግሥት ሠራዊት በየቦታው በሚያደርገው ኃላፊነት የጎደለው የጅምላ ግድያ እና ጭፍጨፋ የንጹሃን ዜጎች ሕይወት በየዕለቱ እንደቅጠል እረገፈ ነው፡፡” ሲልም አክሏል።
በተለይም በምዕራቡ የኦሮሚያ ክፍል፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን ከመንግሥት ትዕዛዝ ተቀብሎ የሚንቀሳቀሰው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊትለ “ፋኖ” የተባለውን ሥም እንደሽፋን በመጠቀም በንጹሃን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እየፈጸመ ነው ብሏል፡፡
ግንባሩ ከተለያዩ ምንጮች አጣርቻለሁ ባለው መረጃ መሰረት፣ ከመስከረም 02/2016 እስከ መስከረም 04/2016 ለተከታታይ ሦስት ቀናት በዞኑ ጊዳ አያና ወረዳ የመከላከያ ሠራዊት አንድ ክንፍ በሆነው ኮማንዶ በተሰኘው ኃይል በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ዘግናኝ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ መስከረም 02/2016 በአንገር ጉትን ወረዳ አራት የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አንድ ቤት ዘልቀው በመግባት “አሳድሩን” ካሉ በኋላ፤ በማግስቱ ጠዋት ላይ ያላንዳች ምክንያት ሙሉ የቤተሰቡን አባላት ገድለው መሄዳቸውን ኦነግ በመግለጫው ጠቅሷል።
በዚሁ ቀን መስከረም 03/2016 በኪረሙ ወረዳ ቡርቃ ሶሩማ ቀበሌ ልዩ ቦታው ቁዬ በተባለ ሥፍራም የሠራዊቱ አባላት በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ተኩስ መክፈቱን በመግለጽ፣ ኹለት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን እና በኹለት ወጣቶች ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል፡፡
ኦነግ አክሎም፤ “ከኹሉም የከፋው እና ዘግናኙ ጥቃት መስከረም 04/2016 ከነቀምት ከተማ እና ከአንገር ጉትን ወረዳ ተነስተው ወደ ጊዳ አያና ወረዳ ሲያቀኑ የነበሩ ንጹሃንን ከመኪና በማስውረድ ዲቾ በተባለ ሥፍራ በጅምላ መረሸናቸውን ነው፡፡” ብሏል፡፡
“በዚህ ግድያ አስካሁን ድረስ 31 ሰዎች መሞታቸውን አረጋጫለሁ፡፡” ያለው ግንባሩ ከሟቾች መካከል በርካታ እናቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ከ11 በላይ ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጿል፡፡
ከሟቾች መካከል ወንድማማቾች እንዳሉበት ያሳወቀው ኦነግ፤ በዚሁ ዕለት በጂዳ ወረዳ ቀርሳ በተባለ ቀበሌ አንድ አባወራ ከነቤተሰባቸው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡
“በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የአገሪቷ መንግሥት በተለይም ከሦስት ዓመታት ወዲህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ታርጋ በመለጠፍ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ገድሎ በዱር በመጣል እና በአውሬ በማስበላት፣ ቤት ንብረታቸውን በእሳት ማቃጠል፣ በአደባባይ መግደል፣ እናቶችን እና ሴቶችን አስገድዶ መድፈር፣ ሰዎችን እንደ እንስሳ በእስር ቤት ማጎር እንዲሁም አውጥቶ በጅምላ መረሸንን የመሳሰሉ ለማመን የሚከብዱ ወንጀሎችን ፈጽሟል።” ነው ያለው።
“ይህ ኹሉ ሰቆቃ በኦሮሚያ ምድር ላይ ተፈጽሞም ተሰምቶም የሚያውቅ አይደለም፡፡” ያለው ኦነግ፤ ይህም የሆነው በዚህ በአምስት ዓመታት ውስጥ በመንግሥት የተፈጸመ ዘግናኝ ወንጀል ነው ብሏል።
“የራስን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ንጹሃን ዜጎችን በየዕለቱ በጅምላ መጨፍጨፍ ከባድ ወንጀል ነው፡፡” ካለ በኋላም፤ “በአገሪቷ በዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ ለደረሰው የዜጎች እልቂት በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡” ሲል ገልጿል።
“በንጹሃን ላይ በየዕለቱ የሚፈጸመውን የተረገመ እና የአውሬነት ተግባር እቃወማለሁ፡፡” ያለው ኦነግ፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ድርጊቱን እንዲያወግዙ እና ስርዓቱ በዜጎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች እያደረሰ ያለውን ግፍ እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡



