ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ድርቅ ተከስቶ፤ ከ19 ሺሕ ሄክታር በላይ ሰብል ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የሰሜን ጎንደር ዞን ገልጿል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰላምይሁን ሙላት፤ በዞኑ በሚገኙ የጃናሞራ ወረዳ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጠለምት ወረዳዎች እንዲሁም የበየዳ ወረዳ እና የተወሰኑ የደባርቅ አካባቢዎች ከግንቦት 15/2015 በኋላ መደበኛ ዝናብ ባለመዝነቡ ለከፋ ድርቅ ተጋልጠዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ከ452 ሺሕ በላይ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን የገለጹት ሃላፊው፤ ከእነዚህ መካከል 202 ሺሕ ያክሉ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አንድ ሺሕ አምስት መቶ ኩንታል በቆሎ የላከ ቢሆንም፤ ተደራሽ የሆነው ለ13 ሺሕ ሰዎች ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ የርሃብ አደጋ በመደቀኑ በሰዎች እና በእንስሳቶች ላይ ተላላፊ በሽታ እየተከሰተ መሆኑንም የገለጹ ሲሆን፤ ከ121 ሺሕ በላይ እንስሳቶች በተለያዩ በሽታዎች የታመሙ ሲሆን፤ 53 ሺሕ ያክሉ እንስሳቶች መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ “በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ሌላ አካባቢ እየሄዱ በመሆናቸው፤ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ ድጋፍ ካላደረገ የሰዎች እና የእንስሳቶች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኹሉም አካል የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደረግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡



