ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በተዋቀረው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ፤ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃይል በሶዶ ወረዳ ሥር የሚገኙ አስር ቀበሌዎችን መቆጣጠሩን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ “ኦነግ ሸኔ ባለፉት ኹለት ዓመታት በሶዶ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወጣ ገባ እያለ ሲንቀሲቀስ የቆየ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን በወረዳ ሥር የሚገኙ አስር ቀበሌዎችን ተቆጣጥሮ ግድያና ዘረፋ እየፈጸመ ነው።” ብለዋል፡፡
በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ከሆኑት ቀበሌዎች መካከል ዱግዳ ገርዬ፣ ዱግዳ ጎሮ፣ ዱባ ጥሙጋ፣ አሽከዴ፣ አማውቴ ላልዬ፣ ሞረጌ፣ ሰመሮ ኤጀርሳ፣ በርበር፣ ቦኖ እንዲሁም አይገዶ የሚባሉት የሶዶ ወረዳ ቀበሌዎች የክልሉ መንግሥት የማይገባባቸውና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
ታጣቂ ቡድኑ “አስር የሚሆኑ ቀበሌዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ገንዘብ ይቀበላል፣ የትጥቅ ፈቃድ ያላቸውን አርሶ አደሮች መሳሪያ ይቀማሉ፣ንጹሃን ሰዎችንም እየገደሉ ነው።” ሲሉ ነው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት፡፡
እንዲሁም በዞኑ መቂ ከተማ በርካታ ነጋዴዎች እና አርሶ አደሮችን በማፈናቀል ወደ ቡታጅራ፣ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና፣ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች ከተሞች እንዲፈናቀሉ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አክለውም፤ በሰኔ 2015 ዱግዳ ጎሮ በተባለ ቦታ ከዚህ በፊት ሞዴል አርሶ አደር ተብለው ሲሸለሙ የነበሩ ጌታቸው አማረ የተባሉ ሰው በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም፤ በነሐሴ 2015 የበርበር ቀበሌ ነዋሪ በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ጠቁመው፤ “ሠበሮ በሚባል ቀበሌ የቀድሞ የቀበሌው ሊቀመንበር 150 ሺሕ ብር፣ ሶልኬ በተባለ ቦታም በተመሳሳይ መክብብ ሽጉጤ የተባሉ የአንድ ታዋቂ ሰው ባለቤትና አንዲት ሴት ሠራተኛቸውን አግተው 100 ሺሕ ብር አስከፍለው ለቀዋቸዋል።” ሲሉ ነው ያብራሩት።
የሶዶ ወረዳ ፖሊስ አዛዠ ኮማንደር አለማየሁ ደነቀ፤ ለኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የሆኑ ከላይ የተጠቀሱት ቀበሌዎች የሸኔ ታጣቂዎች በብዛት እየተንቀሳቀሱባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አክለውም “ቀበሌዎቹን ከሸኔ ታጣቂዎች ነጻ ለማውጣት የወረዳው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የሚሊሻ አባላቶች በጋራ በመሆን እየሰራን ነው።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
“በሶዶ ወረዳ ሥር በሚገኙት አስር ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ታጣቂዎች በመሆናቸው፤ የመንግሥት መዋቅር ወደ አካባቢው ገብቶ እየሰራ አለመሆኑንና ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ናቸው።” ያሉም ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ታጣቂዎቹ በማሕበረሰቡ ላይ ግድያ እና ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
ለአብነትም፤ ጳጉሜ 4/2015 ዱግዳ ጎሮ እና ዱግዳ ገርየ በተባሉ ቦታዎች አንድ ሚሊሻ ሌሊት በጥበቃ ሥራ ላይ እያለ መግደላቸውን በማውሳት፤ “በሰኔ ወር 2015 በተመሳሳይ አንድ ሞዴል አርሶአደር እና ነጋዴ የነበረን ሰው ገድለዋል።” ብለዋል፡፡
“በተጨማሪም ግለሰቦችን አፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ እየወሰዱ ገንዘብ እና መሳሪያ እንዲሰጧቸው እየጠየቁ ነው።” ሲሉ ኮማንደር ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ አክለውም፤ “ችግሩ በፌደራል እና በክልሉ መንሥስታት በኩል የታወቀ በመሆኑ ወደ አካባቢው የመከላከያ ሰራዊት እየገባ ነው።” ካሉ በኋላ፤ “በአጭር ጊዜም አካባቢውን ከሸኔ ታጣቂዎች ነጻ እናደርጋልን።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡



