አርብ መስከረም 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኘው በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ውስጥ ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው በሕገ ወጥ መንገድ የሰፈሩ ከ30 ሺሕ በላይ አባወራዎች፤ ከፓርኩ እንዲወጡ ሊደረግ መሆኑን የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አደም መሃመድ፤ “በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ጣቢያ ከሶማሌ እና ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ መጠለያ ጣቢያው ገብተው የሰፈሩ ሰዎችን፤ ከጣቢው እንዲውጡ ልናደርግ ነው፡፡” ሲሉ አውስተዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ከ30 ሺሕ በላይ አባወራዎች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ “የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው በሕገወጥ መንገድ ወደ መጠለያ ጣቢያው የገቡት ሰዎች አብዛኞቹ፤ በመጠለያ ጣቢያው አዋሳኝ አካባቢ ሲኖሩ የነበሩ የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ከመጠለያ ጣቢያው በሕገወጥ መንገድ ሰፍረው የሚገኙት በግጭት ምክንያት ከሌላ ቦታ የተፈናቀሉ ሳይሆኑ ተጨማሪ የእርሻ መሬት ፈልገው የገቡ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ባለሃብቶችም ሰፍረው እንደሚገኙ አክለዋል፡፡
ሕገወጥ ሠፋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በዝሆኖች መጠለያ ጣቢያ ቅጥር ገቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ሰርተው፣ ትዳር መስረተው በተጨማሪም ሰፊውን የመጠለያ ጣቢያውን ክፍል በማረስ ራሳቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
“እነዚህን ሰዎች ከመጠለያ ጣቢያው ስናስውጣቸው፤ ምንም አይነት ካሳ አንከፍልም፡፡” ያሉት አደም፤ “ሰርተውት የነበረውን የመኖሪያ ቤትም በማፍረስ የዝሆኖች መጠለያ ቅጥር ግቢው ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል እናደርጋለን፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በ2013 በጣቢያው ውስጥ የሸራ ቤት ሰርተው ሲኖሩ ከነበሩት መካከል፤ ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑ የአባውራ ቤቶችን ማፍርሳቸውን እና ሰዎቹንም ለማስወጣት ሙከራ አድርገው ተቋርጦ መቆየቱንም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል “ከፓርኩ አጠቃላይ ይዞታ ከ200 ሄክታር በላይ የሚሆነው ለኢንቨስትመንት ተስጥቶ እየታረሰ ነው፡፤” ያሉት ኃላፊው፤ “ድርጊቱን እንዲያስቆሙልን መስከረም 2016 ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ያስገባን ቢሆንም፤ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠንም፡፡” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሕገወጥ ሰፋሪዎች ወደ መጠለያ ጣቢያው መስፈር የጀመሩት ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ መሆኑን ጠቁመው፤ “ለመከልከል ስንሞክርም ሰዎቹ አብዛኞቹ የታጠቁ በመሆናቸው እና የግድያ ሙከራ በማድረጋቸው ከአቅማችን በላይ ሆነዋል፡፡” ብለዋል፡፡
በዚህም “እነዚህ ሕገወጥ አካላት እንዲነሱ የሚያደረጉት በፌዴራል መንግሥት በኩል የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡



