ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሰሃላ ሰየምት ወረዳ በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ በመምጣቱ፤ በርሃብ ምክንያት የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማስረሻ መኮነን፤ “በወረዳው በተከሰተው አስከፊ ድርቅ በርሃብ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እያለፈ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
“በወረዳው ከ8 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚህ ውስጥ ከ7 ሺሕ 300 መቶ ሄክታር መሬት በላይ ሰብል ሙሉ ለሙሉ በመውደሙ በነዋሪዎች ቤት ምንም አይነት የምግብ ግብዓት የለም፡፡ በዚህም እስካሁን የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል ሲሉ” ተናግረዋል፡፡
ከነዋሪዎቹ በተጨማሪ በእንስሳቶች ላይ ከፍተኛ ርሃብ በመኖሩ የሞት መጠናቸው እየጨመረ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡ በድርቁ ምክንያት ለእንስሳቶች የሚሆን ምንም አይነት ግብዓት ባለመኖሩ እስካሁን አራት ሺሕ ገደማ እንስሳቶች መሞታቸውን አመላክተዋል፡፡
መንግሥት እና አንዳንድ ግብረሰናዊ ረጅ ድርጅቶች በተወሰነ መልኩ ለሰዎች የሚሆን የምግብ ግብአት እያቀረቡ ቢሆንም፤ ለእንስሳቶች ግን ምንም አይነት ድጋፍ ያደረገ አካል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ “በድርቁ ለተጎዱ ማሕበረሰቦች በተወሰነ መልኩ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፤ በቂ አይደለም፡፡ እስካሁን ምንም አይነት እርዳታ ያልተደረገላቸው ሰዎች አሉ፡፡” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘም፤ በድርቁ ምክንያት በሰዎች እና በእንስሳቶች ላይ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች መከሰታቸውን አክለዋል፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በተወሰነ መልኩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል በትኩርት ሊመለከተው እንደሚገባ ጠቁመው፤ በሰዎች እና በእንስሳቶች ላይ የተከሰተውን ተላላፊ በሽታ መከላከል ካልተቻለ አደጋው የከፋ እየሆነ እንደሚመጣ አሳስበዋል፡፡
በወረዳው በተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 37 ሺሕ 600 ሰዎች በላይ መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል፡፡


