ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ሕጻናት ልዩ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት መካከል ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱን በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አቡባካር ካምፖ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤል የተፈራረሙት ሲሆን፤ በዚህም ዩኒሴፍ በአገሪቱ ዉስጥ ያሉ ኹሉም ነዋሪዎች ለዲጂታል መታወቂያ መርሀ ግብር እንዲመዘገቡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ስምምነቱ በችግር ዉስጥ ያሉ የዩኒሴፍ ተጠቃሚዎችን እና ሕጻናትን ልዩ ዲጂታል መታወቂያ በመስጠት መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንደሚረዳቸውም ተመላክቷል።
በ2015 በጸደቀው የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ውስጥ፤ የሕጻናትን መታወቂያ የማግኘት መብት የሚያረጋግጥ ክፍል መካተቱን ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሕጻናት በአንድ አካባቢ ተወልደው ወደ ሌላ አካባቢ በሚዘዋወሩበት ጊዜ ማንነታቸው እንዲታወቅ መብት እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት፤ ከ4 ዓመት ጀምሮ ያሉና የጣት አሻራቸው የማይነበብ ሕጻናትን ዲጂታል መታወቂያን ለመስጠት መታቀዱን የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 90 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡



