ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ድረስ በአማራ ክልል የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአግባቡ የመማር ማስተማር ስርዓት ባለመጀመራቸው ሴት ሕጻናቶች ለያለእድሜ ጋብቻ እና ጠለፋ እየተዳረጉ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ ከ2013 ጀምሮ እስከተያዘው 2016 ሩብ ዓመት የትምህርት ስርዓቱ በአግባቡ ባለመጀመሩ ሴት ሕጻናቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቁጭ ሲሉ፤ በወላጆቻቸው በኩል “ከወንዶች ጋር ይባልጋሉ ወይም ጾታዊ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል” በሚል የተሳሳተ አመለካከት በመኖሩ፤ ልጆች እድሜያቸው ለጋብቻ ሳይደርስ እና ፈቃደኞች ሳይሆኑ እንዲያገቡ እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የአማራ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ግንዛቤ ንቅናቄ ማስፋፊያ ባለሙያ ሳዲያ ኡስማን፤ የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ አሁን በክልሉ በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው የትኩስ ልውውጥ ምክንያት የትምህርት ተቋማቶች ዝግ በመሆናቸው ሕጻናቶች በያለእድሜ ጋብቻ እንዲያገቡ እየተደረጉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህም በክልሉ በ2013 ከ1 ሺሕ 900 በላይ፣ በ2014 ከ1 ሺሕ 100 በላይ እንዲሁም በ2015 ከ1 ሺሕ በላይ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ያለዕድሜ ጋብቻ እንደተፈጸመባቸውየገለጹ ሲሆን፤ በ2015 ዓመት 91 ሴቶች መጠለፋቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጸም ምክንያት ከሚሆኑት መካከል የኮሮና ቫይረስ፣ የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር እንደሚገኙበት አንስተዋል፡፡
አክለውም “በማህበረሰቡ በኩል ያለው የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም፤ በገጠራማ ቦታዎች የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ካለመኖሩ የተነሳ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሲቀመጡ በወላጆቻቸው አማካኝነት ያለዕድሜያቸው እንዲያገቡ ይደረጋሉ።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻ በሚፈጽሙ ወላጆች ላይ ቢሮው ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ከእስራት ቅጣት ጀምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ቢሆንም፤ በድብቅ የሚፈጸሙ ያለዕድሜ ጋብቻዎች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አክለውም በ2014 እና 2015 ብቻ ከያለእድሜ ጋብቻ እና ጠለፋ በተዘዋዋሪ 2 ሺሕ 980 የሚሆኑ ሴቶች እና ወንድ ሕጻናቶች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል 2 ሺሕ 669 ያክሉ አዋቂ ሴቶች ሲሆኑ፣ 311 ያክሉ ደግሞ ከ18 ዓመት በታች የሆናቸው ሕጻናት ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
የአስገድዶ መደፈር ከደረሰባቸው ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ሴቶች መካከል አንዱ የ16 ዓመት ወንድ ሕጻን ነው ብለዋል።
ከላይ የተገለጹት ቁጥሮች በሴቶችና ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል የተሰበሰቡ መረጃዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ብዙ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ደርሶባቸው ደብቀው ሳይናገሩ የቀሩ መኖራቸውንና መናገር ፈልገው ወደ ሴቶች ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ መምጣት ያልቻሉ በርካታ ናቸው ብለዋል።
ጥቃቱ የሚፈጸምባቸው በታጣቂዎች፣ በወጣቶችና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ መሆኑን አክለዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ እና ጠለፋ በአብዛኛው የሚካሄድባቸው የክልሉ አካባቢዎች በምስራቅ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን መሆኑን ጠቁመው፤ በክልሉ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ያለው ግጭት ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል።
ለአብነትም ጾታዊ ጥቃት በብዛት ይፈጸምባቸዋል ከሚባሉት ቦታዎች መካከል የሰሜን ጎንደር ዞን አንዱ ሲሆን፤ የዞኑን ሴቶችና ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ መምሪያ አዲስ ማለዳ አናግራለች።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶችና ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ የሆኑት ውባለች አድማሱ፣ በ2014 እና 2015 ብቻ 586 ሴቶች ያለእድሜ ጋብቻ ተፈጽሞባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም በ2014 እና 2015 በኹለት ዓመታት ብቻ 188 አስገድዶ መደፈር ተፈጽሟል ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ኹለቱ የዘጠኝ እና የ16 ዓመት ሕጻን ወንዶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ መሰል ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመው በሰሜን ጎንደር ዞን ሥር በሚገኙ በኹለት ከተማ አስተዳደሮችና በስድስት ወረዳዎች መሆኑን አክለዋል።
አያይዘውም በ2014 እና በ2015 በኹለት ዓመታት ብቻ 23 ጠለፋዎች መፈጸማቸውን አመላክተዋል።
በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የሙሉ ማተንት የተሰኘ የእናቶች ማዋለጃ ማዕከል ቡድን መሪ ሳምሶን አዳነ በበኩላቸው፤ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወደ ማዕከላቸው የሚመጡ በርካታ ሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሴቶች ለማህጸን በር ካንሠር እና ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጋላጭ አድርጓቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በርካታ ሴቶች የስነልቦና ቀውስ እንደሚያጋጥማቸውም ጠቁመው፤ የሚመለከተው አካል ትኩርት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ አማካሪ የሆኑት መቅደስ መለሰ፤ “ያለእድሜ ጋብቻ እና ጠለፋ እየተስፋፋ የመጣው በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር አማካኝነት ተማሪዎች በየቤታቸው በመዋላቸው እና ያለእድሜ ጋብቻ ሊፈጸምባቸው መሆኑን ሲሰሙ ለመምህራኖቻቸው የሚያሳውቁበት እድል ባለመኖሩ ነው” ብለዋል።
አንዳንድ ሕጻናቶች በወላጆቻቸው አማካኝነት ያለእድሜ ጋብቻ ሊፈጸምባቸው መሆኑ በሰሙበት ወቅት ለሴቶች ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አመልክተው ያለእድሜ ጋብቻ ፈጻሚ ወላጆችን ይዘው ለሕግ ካቀረቧቸው በኋላ፤ በሕግ በኩል የሚፈረድባቸው ቅጣት አናሳ መሆን ለድርጊቱ መስፋፋት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ የሚፈጽሙ አካላት ላይ ክስ ለመመስረትና ጋብቻውን ለማቋረጥ የሕግ አካላት ወደ ወላጆች ቤት በሚሄዱበት ወቅት ሊያጋቧት ያሰቧትን ልጅ በመደበቅ ከ18 ዓመት በላይ እድሜ ያላትን ሴት እንደሚድሩ በማስመሰል የክሱን ሂደት የሚያቋርጡ በርካታ ወላጆች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የሚኖሩ ሰጠአርጌ ምንገሻ (ለደህንነት ሲባል ስማቸው የተቀየረ) ልጃቸውን በያለእድሜ ጋብቻ መዳራቸውን ነግረውናል።
ልጃቸው ለምን በያለእድሜ ጋብቻ እንደዳሩ ሲጠየቁ፤ “ልጄን የማሳደግና የማስተማር አቅሙ ስለሌለኝ፤ ልጄን ያስተምሩልኛል፣ ያሳድጉልኛል አቅም አላቸው ብየ ላመንኩት ሰው እንድታገባ አድርጊያለሁ” የሚል ምክንያታቸውን ነግረውናል።
“በልጄ ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት አያሳስበኝም፤ የሚታሳስበኝስ ልጄን የማበላት፣ የማለብሳት ሳጣ ነው” ያሉት ሰጣርጌ፤ “ትዳር እና ልጅ በልጅነት ነው” በሚለው እሳቤ እንደሚያምኑም ይናገራሉ።
ሰጣርጌ ልጃቸውን የዳሩት በ2015 ጥር ወር አካባቢ በ13 ዓመቷ ነው። ልጃቸው ሊድሯት መሆኑን ስትሰማ ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ በማውራቷ የታሰበውን ሰርግ ለማቋረጥ የጸጥታ አካላት ከቤታቸው ድረስ ሂደው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በመሆኑም “ልጄዎትን በያለእድሜ ጋብቻ ሊድሩ መሆኑን ሰምተናል ለአቅመ ጋብቻ መድረሷን ለማረጋገጥ መመርመር ይገባታል እና ወደ ጣቢያ ይዛችኋት ኑ” የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ያወሳሉ።
ሰጣርጌም ከፖሊስ የመጣላቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው፤ የምታገባዋን የ13 ዓመት ሕጻን ልጅ ወደ ሌላ ቦታ አስወስደው በመደበቅ ታላቅ የ21 ዓመት ልጃቸውን ወስደው ማስመርመራቸውን ነግረውናል።
እንዲህ በማድረጋቸው ያስደሰታቸው ሰጣርጌ ኹኔታውን ሲያስታውሱ፤ “ልጄን እነሱ የሚያሳድጉልኝ ይመስላሉ አትድራትም ሲሉ! ታላቋን ልጄን ወስጄ ሸወድኳቸው” በማለት ሰለኹኔታው ይገልጻሉ።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ በማሕበረሰቡ ደረጃ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ለያለእድሜ ጋብቻ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ማወቅ አያዳግትም።
በዘንድሮው 2016 ዓመት በክልሉ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር በዚሁ ከቀጠለ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ረቀው ስለሚቆዩ በወላጆቻቸው አማካኝነት ያለእድሜ ጋብቻ እንደሚፈጸምባቸው ይገመታል።
ለአብነትም በአማራ ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች እስካሁን አለመመዝገባቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በክልሉ ለ2016 የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከተያዘው ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካከል የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ አማካኝነት ምዝገባ ያልተካሄደባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰውም፤ “የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች መቼ ምዝገባ መካሄድ እንዳለበት እየተወያዩ መሆኑን ገልጸዋል።



