በመዲናዋ የሚገኙ ነዋሪዎች በየጊዜው የቤት ኪራይ እንዲጨምሩና እንዲለቁ መደረጋቸው እንዳማረራቸው ገለጹ

ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች በየጊዜው የቤት ኪራይ እንዲጨምሩና እንዲለቁ መደረጋቸው ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተጨምሮ እያማረራቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ መስተዳደር በየጊዜው አከራዮች የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩና ተከራይን እንዳያስወጡ መመሪያ ቢያወጣም፤ ተግባራዊነቱ ግን እምብዛም እንደሆነ ተከራዮቹ በምሬት ገልጸዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይም አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አነጋግራለች።

በቦሌ ቡልቡላ ልዩ ሥሙ ማርያም ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ እና የኹለት ልጆች እናት የሆነችው ሴት፤ “አከራያችን ወረቀት ሰጠችን ምን እንደሆነ እንኳን ለማንበብ ጊዜ ሳትሰጠን አስፈርማን ሄደች። ወረቀቱ ላይ የነበረው ቤቱን ማደስ ስለምትፈልግ በኹለት ወር ጊዜ ዉስጥ ሙሉ የግቢው ተከራዮች እንድንወጣ ነበር ያስፈረመችን” ብላለች።

አክላም “በግቢው ዉስጥ ያለነው ኹላችንም የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነን ይሄ ኹሉ ሰው በአንድ ጊዜ ገቢውን ያገናዘበ፤ ለሥራው አመቺ የሆነ ቦታ ማግኘት አይችልም። ኹሉም ግራ ተጋብቶ ነው ያለው” በማለት ገልጻለች።

በመጨረሻም መንግሥት አከራዮች የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩና ተከራዮችን እንዳያስወጡ መመሪያ ቢያወጣም፤ አሁን ደግሞ የመመሪያው ጊዜ ባልተጠናቀቀበት ኹኔታ እንዲወጡ መገደዳቸውን አግባብ አይደለም ስትል ተናግራለች።

በመዲናዋ የሚገኙ አከራዮች ቤቱ ለሌላ ሥራ ይፈለጋል፣ ቤተሰብ ከውጭ መጥቶብኛል፣ ለእድሳት በሚሉ ሰበቦች ተከራዮችን እንደሚያስወጡ ይነገራል።

በተመሳሳይም ነዋሪነቱን ሾላ ያደረገ በሕክምና ዘርፍ ላይ የተሰማራ ወጣት ከሚከፈለው ደሞዝ አንጻር በዕቃዎች ላይ ዕለት ከዕለት ከሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ሆኖ፤ የቤት ኪራይ ዋጋ ነገሮችን ከአቅሙ በላይ እንዳደረጉበት ይገልጻል።

ይሄው ወጣት አክሎም “በተለይ አዲስ አበባ ያሉ የጤና ሙያተኛ ሰልጣኞች ችግሩን መቋቋም አቅቷቸው ለከፋ ቀውስ እየተጋለጡ ነው። ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወደ መጡበት እየተመለሱ ነው” ሲል ገልጿል።

የከተማዋ አስተዳደር በቤት ባለቤቶች ላይ ያወጣው አዲስ የንብረት ባለቤትነት ታክስ ምጣኔም ጫናው በይበልጥ በተከራዮች ጫንቃ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ችግሩን እንዳወሳሰበው መረጃዎች ያመላክታሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 3/2015 ባወጣው መመሪያ መሰረት ለሚቀጥሉት 6 ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት የማይቻል መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በግል ከሚደረግ ስምምነት ውጪ ማንኛውም አከራይ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት እንደማይቻል መግለጹ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here