
“400 የኢቢሲ ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው” ያጋለጠው ወገን አበበ ከሥራ መባበሩን ተከትሎ ያላግባብ ተባርሬያለሁ ብሎ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚያስችለውን ውሳኔ ለመወሰን፤ በዛሬው ዕለት ቀጠሮ በነበረው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት “ጉዳዩን መርምሮ ስላልጨረሰ” በማለት ለመጋቢት 2 ቀን 2016 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
“ያለአግባብ ከሥራዬ ተሰናብቻለው” ያለው ወገን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ)ን ይግባኝ ለመጠየቅ የሚያችለውን ውሳኔ ለማግኘት የነበረውን ችሎት ተከትሎ በፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት “እኛ እየተጉላላን ነው” ሲሉ የወገን አበበ ጠበቃ ሰለሞን አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ደንበኛቸው “ለተደጋጋሚ ቀጠሮ በመዳረጉ አዲስ አበባን ለመልቀቅና ወደ ክፍለ አገር ሄዶ ከቤተሰቦቹ ጋር እንዲኖር አድርጎታል” ያሉት ጠበቃው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ወገንን የከሰሰው እና ያሰናበተው የዓመት እረፍት ላይ ሆኖ እራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ መሆኑን ጠበቃው አስታውሰዋል።
ይግባኝ ማስፈቀጃ መጠየቅ ያስፈለገውም የተቋሙ (ኢቢሲ) ውሳኔ በተሰጠ በሰላሳ ቀናት ዉስጥ ይግባኝ አቤቱታ መቅረብ እያለበት፤ በጥበቃ ሠራተኞች ጭምር ወደ ተቋሙ አትገባም ተብሎ “ይህ የአንድ ወር ጊዜ በማለፉ” ነው ሲሉ ጠበቃ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
“በመጪዉ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ይግባኙ እንዲቀርብ ከፈቀደ የይግባኝ አቤቱታችንን በዝርዝር እንናያይዝና ወደ ክርክርሩ ዋነኛ ጉዳይ የምንገባ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

በተመሳሳይ ወገን ለአዲስ ማለዳ እንደገልጸው “የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ከጥቅምት 20 ቀን 2016 ጀምሮ ሲሆን እስከ አሁን ይግባኝ ለመጠየቅ የሚያስችለን ውሳኔ ለማስወሰን ነው እየጠበቅን ያለነው። ጠበቃዬም በራሱ በጎ ፈቃድ ነው እያገዘኝ ያለው” ብሏል።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ባለማሳለፉ “ችግር ላይ ነኝ” ያለ ሲሆን ሌሎች ቦታዎች ላይም ሥራ ማግኘት የምችልበት ሁኔታ አነስተኛ ነው ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ለዚህም መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ መስፈርቶቹን አሟልቶ ፈተናውን አልፎ ለተግባር ፈተና በተጠራበት ወቅት ወደ ጊቢው ሊገባ ሲል መከልከሉን አንስቷል።
“በኢቢሲ ምክንያት ነው ወይ ብዬ ብጠይቅም ምላሽ አልሰጡኝ። በመጨረሻም እዛ ግቢ ውስጥም እንዳልገባ ተከለከልኩ” ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሠው ሐብት አስተዳደር ክፍልም “ገና ምን አይተህ ሌላ ቦታም እንዳትሰራ እናደርግሃለን” የሚል ዛቻ ደርሶበት እንደነበረም ጨምሮ ገልጿል።
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገለው ወገን አበበ በኢቢሲ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ “400 የሚሆኑ ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ” እንዳላቸው አጋልጠሃል በሚል ከስራ መባረሩን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
አዲስ ማለዳ ለተቋሙ እና ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የተላኩትን ደብዳቤዎች “ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አላቸው” ከተባሉት ሰዎች ስም ዝርዝር ጋር መመልከቷን ማስታወቋ አይዘነጋም።


