በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አርዳ ወረዳ የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን መኖር ከባድ እንደሆነባቸው እና በአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ድብደባ እንዲሁም መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
በደህንነት ስጋት ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት “ተወልደን ባደግንበት ቦታ እና አገር በማይገባ እና በአፈ ታሪክ ምክንያት የመኖር ህልውናችንን እያጣን ነው፤ እየተሰደብን እየተገለልን አልፎ ተርፎም እየተደበደብን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል።
አክለውም ከስራ እስከ መባረር ድረስ የከፋ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹ ሲሆን “በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ መምጣቱን” በምሬት ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአርዳ ወረዳ በመምህርነት የሚያገለግል ግለሰብ “በመንገድ ሳልፍ ይሰድቡኛል፣ ይባስ ብለው ተከታትለው ደበደቡኝ የሞትኩ ሲመስላቸው ጥለውኝ ሄድ ከብዙ ስቃይ በኋላ ትንሽ ተሻለኝ” ብሎ አሁንም በደረሰበት ድብደባ ጉዳት እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ከሚኖርበት በመሸሽ ተደብቆ እንደሚገኝ የሚገለጸው “ሰለባ”፤ ህክምና ማግኘት እንዳልቻለ እና ይባስ ብሎ ከስራው መባረሩንም አያይዞ ገልጿል።
አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን አርዳ፣ መቄት እና ላስታ ወረዳዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ቤተ እስራኤላውያን እየተገለሉ እና እየተሰደቡ ስለመሆኑ መረጃ የደረሳት ሲሆን በርካታ ቤተ እስራኤላውያን በሚኖሩበት አማራ ክልል ጥቃቱ እየተስፋፋ መሆኑ ተመላክቷል።
አዲስ ማለዳ የደረሳትን ጥቆማ መነሻ አድርጋ ከአካባቢው የፖሊስ አካላት ስለሁኔታው የአርዳ ወረዳ አካባቢ ፖሊስ ጠይቃ “እስካሁን እንደዚህ አይነት ቅሬታም ሆነ ጥቆማ እኛ ጋር አልመጣም፤ ሁሉም በሰላም እና በመከባበር ነው የሚኖሩት” የሚል ምላሽ አግኝታለች።
በአንጻሩ ድብደባና ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች በጣም በተደጋጋሚ ቅሬታ እና አቤቱታ ያሰሙ ቢሆንም “ፖሊሶቹም ሆኑ የጸጥታ ሀይሎች በተመሳሳይ ሁኔታ እንደማይቀበሏቸው እና ምንም አይነት ጥበቃ እንደማያደርጉ” ተናግረዋል።
አክለውም በየሄድንበት “ሰላቢው መጣ፣ እነዚህ ናቸው ሰው የሚበሉት የሚል ጸያፍ ቃላቶችን ይናገሩናል፤ በእናንተ ምክንያት እገሌ ታሟል በቡዳ በልታችሁታል በማለት ይወነጅሉናል” ሲሉም ያሉበትን ከባድ ሁኔታ አስረድተዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጫሒት ከተማ ቀበሌ 02 ስላሴ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራ ታሕሳስ 8 ቀን 2015 “እህቴን ቡዳ ሆነህ የበላሀት አንተነህ” በማለት በክላሽ ጠመንጃ ሰው መግደሉ ተሰምቷል። ጉዳዩ በክርክር ቆይቶ መጋቢት 6 ቀን 2016 በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትህ መምርያ መረጃ አመላክቷል።
ከዚህ ቀደም በነሐሴ ወር 2015 ላይ የእስራኤል መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአይሁድ ዘር ያላቸው ወገኖች የሚያነሱትን ቅሬታ የሚከታተልና የመፍትሔ ጉዳይ የሚያቀርብ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙ ይታወቃል። በመሆኑም በአዲስ አበባ እና በጎንደር ወደ እስራኤል ለማቅናት በሚጠባበቁ ቤተ እስራኤላውያን የኢሚግሬሽን ፈተናዎች ላይ እንደሚያተኩር እንዲሁም የጥናት ግኝቱን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያቀርብ ተጠቁሞ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁን ሰአት በአካባቢው ምንም ቅሬታ ሰሚ አካል እንደሌለ እና የበይነመረብ ግንኙነት በመቋረጡ ወደ እስራኤል ኤምባሲም ሆነ ይሟገትላቸዋል ወደተባለው ተቋም የእስራኤል መልክተኛ መገናኘት አለመቻላቸውን የሰሜን ወሎ አርዳ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ቤተ እስራኤላውያን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


