ፖለቲከኛው በቴ ኡርጌሳ “በጸጥታ አካላት” ከተያዘ በኋላ ነው የተገደለው- የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት

0
2721

ግድያው “ባልታወቁ ሰዎች” የተፈጸመ ነው- የኦሮሚያ ክልል መንግስት

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ስፍራቸው በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ መገደላቸው ታውቋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው “ሸኔ” ወይም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ብሎ የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በኩል ባወጣው መግለጫ በቴ ኡርጌሳ በመቂ ከተማ ካረፉበት ሆቴል እኩለ ሌሊት ላይ “በጸጥታ አካላት” ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል ሲል ገልጿል። 

በቴ ኡርጌሳ አመራር የሆኑበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ግድያውን በተመለከተ የራሱን ምርመራ መጀምሩን አስታውቆ፤ በንቃተ ህሊና ከፍ ያሉ የኦሮሞ የፖለቲካ እና የባህል ሰዎች ላይ ያለምክንያት እና ያለፍርድ መገደል “ኦሮሞን ለዓመታት እና አስርት አመታት ጸጥ ለማሰኘት ስልታዊ እና ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኞች ሳይታወቁ የፖለቲካ አቋም ልዩነት በመኖሩ ብቻ ወደመንግስትም ሆነ ሌላ አካል የሚጠቆሙ ጣቶች አግባብ አይደሉም በማለት ግድያውንም እንደሚያወግዝ በመግለጫ አስታውቋል። 

አዲስ ማለዳ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የፖለቲከኛው በቴ ኡርጌሳ ግድያ ከአንድ የቤተሰብ አባላቸው ጋር ከነበረ የግል ግጭት ጋር እንደሚያያዝ የሚገልጹ ጽሁፎችን ተመልክታለች። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መግለጫ እንደሚለው በቴ ወደ መቂ ከተማ የተጓዙት እናታቸውን ለመጠየቅ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ኦነግ ስለዚህ ሁኔታ ምንም አላሉም። 

  

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ግን ከግድያው በኋላ “የጸጥታ ኃይሎች አስከሬኑ እንዳይመለስ እየከለከሉ እና በኋላም ደግሞ ተጨማሪ የአስከሬን ምርመራ እንዳይካሄድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። አካባቢው [መቂ] የመገናኛ መስመሮችም ተቋርጠዋል” በማለት ገልጿል። 

ግድያው “ባልታወቁ ሰዎች” ተፈጽሟል ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ደግሞ በፖለቲከኛው ግድያ ዙሪያ ከተሟላ ምርመራ በኋላ መረጃ ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “በፈሪ የጭካኔ ድርጊት ከእኛ ተወስዶ የእምነቱን ኃይል እና የባህርይ ጥንካሬን በሚፈሩ ሰዎች ጸጥ ተደረገ” በማለት የበቴ ኡርጌሳን ግድያ ገልጿል። 

የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በኩል በተሰራጨው መግለጫም በቴ ኡርጌሳ በተደጋጋሚ “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር እና በድብቁ ‘ኮሬ ነጌኛ’ አማካኝነት” መታሰራቸውን አመልክቷል። 

በየካቲት ወር አንቷን ጋሊልዶ ከተባለ ፈረንሳያዊ ጋዜጠኛ እና በመንግስት ሁከት ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል በሚል ከተጠረጠረ ግለሰብ ጋር በስካይላይት ኢትዮጵያ ሆቴል ከበቴ ኡርጌሳ ጋር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ተገናኝተው በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።   

ነጻና ገለልተኛ ምርመራ

በቴ ኡርጌሳ አባል የነበሩበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር “ሁሉም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ሰላም ወዳድ ህዝብ አፋጣኝ ገለልተኛ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ብሏል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ከግድያው በኋላ በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል የነበሩት በቴ ኡርጌሳ መገደላቸውን ተከትሎ ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሁለቱም የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ባለስልጣናት አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ” በማለት ጠይቀዋል።

የአሜሪካ መንግስትም የግጭት አዙሪትን ለማቆም ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማስፈን መሰረታዊ በመሆኑ የበቴ ኡርጌሳ ግድያን በተመለከተ የተሟላ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here