የቨርችዋል ኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ እህት ኩባንያ የሆነው ሮሐ ኢቬንትስ በሱሉልታ ከተማ በሚገኘው ቀነኒሳ ሆቴል ዉስጥ፣ በኻያ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አስራ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር፣ ለኹለት ዓመት የኪራይ ኮንትራት በመያዝ በዓይነቱ ለየት ያለ ከኤሌክትሮኒክስ እና ከመጠጥ ነፃ የሆነ የአዋቂ እና የሕፃናት መዝናኛ ግንባታዉ ተጠናቀቀ።
የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አማራጮችን በተለይም የኤሮቢክስ፣ የቼዝ እና የዋና ስፖርቶችን በግሎ እና ከያያ ቪሌጅ ጋር በመተባበር እንደሚሰጥም አስታውቋል። ሪዞርቱ ያረፈበት ቀነኒሳ ሆቴል የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶችም አያይዞ ይሰጣል።
በተለይም ለሕፃናት እንደ እግር ኳስ ያሉ የጋራ መጫወቻዎችን የያዘ ሲሆን ታሪክ፣ ግበረ ገብ፤ ተረት፣ ግጥም፣ ስዕል፣ የሙዚቃ መሣሪያ ትምህርት፣ አገረኛ ቋንቋ፣ የውበት ሳሎኖችን፣ ስቴሽነሪ፣ ምግብ እና መጠጥ አማራጮችን ጨምሮ በዓይነቱ ለየት ያለ አማራጭ ይዞ መቅረቡንም የሮሐ ኤቨንትስ ዳይሬክተርና መሥራች አሸናፊ ጉታ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በሮሐ ኤቨንትስ የሚዘጋጅ እና ቅዳሜ እና እሁድ ላይ ሙሉ የቤተሰብ ጥቅል በመያዝ ይጀመራል የተባለው አገልግሎቱ፣ በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እያመጣ ያለውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ የተቀረፀ መሆኑንም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
‹‹በአሁኑ ዘመን የማይዘወተሩ እንደ አባሮሽ እና አኩኩሉ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች የሚጫወቷቸውን የድሮ ጨዋታዎችን ለመመለስ የተለያዩ ዝግጅቶች እናደርጋለን›› ሲሉ አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹በዘመናዊነት ውስጥ የተዋጡት ልጆቻችን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያገኙ በቴክኖሎጂ ምክንያት ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ከማኅበራዊ ሕይወት ያላቸዉን ርቀት በመገንዘብ የአካልም የመንፈስም ጥንካሬ ለመስጠት ዓላማዉ ያደረገ ሪዞርት እንዲሆን አድርገናል›› ሲሉ አሸናፊ ገልፀዋል።
ፕሮግራሙን ለማጥናት 3 ዓመት እንደፈጀ እንዲሁም ጥናቱን መሬት ለማዉረድ እስከ አሁን 3 ወር ጊዜ እና ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳስወጣ ለማወቅ ተችሏል። ጥር 15/2012 በይፋ እንደሚመረቅ አሸናፊ የገለጹ ሲሆን፣ በቅድመ ምዝገባም ከ400 ሰዎች በላይ ተመዝግበዉ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
ሮሐ ኤቨንትስ እንዳስታወቀው፣ በሱሉልታ የሚጀመረው ፕሮግራም በቀን አንድ ሺሕ ሰው ማስተናገድ የሚችል ቦታ ሲሆን ከኻያ ስምንት ሰዎች በላይ የሥራ እድል እንደፈጠረ አስታዉቋል። ከቀነኒሳ ሆቴል ጋር ለኹለት ዓመት በሚቆይ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ በሱሉልታ ከተማ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ማስፋፊያ የማድረግ እቅድ መያዙንም አሸናፊ ጠቅሰዋል።
የመክፈቻ ፕሮግራሙ አካል የሆነው በማኅበራዊ ሚዲያው በተለይም በፌስቡክ እውቅና ያገኘውን ‹‹የ90ዎቹ ልጆች›› አባል የሆኑ አምስት መቶ ልጆች በመጋበዝ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012



