በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በደረሰው ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የገለጸው የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈትቤት ነው።
ጽህፈት ቤቱ ከአካባቢው ባለሥልጣናት አገኘሁት ባለው መረጃ ተመስርቶ ባወጣው የሁኔታዎች መግለጫ ላይ ነው በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አሃዝ እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ያመለከተው።
ባለፉት ቀናት በተደረጉት የፍለጋ ጥረቶች በአደጋው ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ ሰዎች ቁጥር 257 የደረሰ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ስጋታቸውን መግለጻቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አመልክቷል።
እሁድ ሐምሌ 14 እና ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተቀብረው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ዛሬም ለአራተኛ ቀን እየተካሄደ ነው።
በአደጋው የቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በነብስ አድን ስራ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወቅ ነው፡፡



