ሐምሌ 18 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር በልማት ሰበብ እየፈጸመ ያለውን ኢ- ህገመንግስታዊ ድርጊት ሊያቆም አልቻለም ሲል የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ካውንስል ከሷል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው የኩሪፍቱ ማዕከል ከህግ ውጪ በሀይል በተወሰደ እርምጃ መነጠቁን አስመልክቶ የፍትህ ጥያቄ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አቅርቦ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ካውንስሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በደብዳቤ እና በአካል ሲወያይ ቆይቶ ይዞታውን ማልማት አልቻሉም በሚል ቦታው እንደተወሰደበት ነው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው፡፡
አክሎም ቤተ ክርስቲያኒቱ የፍትህ ጥያቄ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያቀረበች ቢሆንም ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣት ነው ካውንስሉ የጠቆመው፡፡
ካውንስሉ አክሎም በሀይል የተወረረው መሬት እና የታጠረው አጥር እስኪፈርስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንታገላለን ብሏል፡፡
ጉዳዩ የእምነት ብዝሃነት ባለበት አገር የሃይማኖት ነጻነትን የሚገፍ ተራ እርምጃ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረድቶ ከቤተክርሰቲያኗ ጎን ሊቆም ይገባል ሲል በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኝ በሕጋዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኗ ከተላለፈ የመሬት ይዞታ ላይ 40 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆነውን በግድ ተነጥቀናል፤ ይዞታውን በሀይል በመቀማት ለሁለት ግለሰቦች እንደተሰጠ እና ጉዳዩን አስመልክቶ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይዞታው የቤተ ክርስቲያኗ እንደሆነ ተወስኖ ነበር ማለቱን አዲስ ማላዳ መዘገቧ አይዘነጋም፡፡


