ፓርቲው “መንግስት በቀጥታ እና በንቁ ሁኔታ ጣልቃ መግባት ካልቻለ፤ “ከጥልቅ ድህነት መውጣትም ሆነ ማህበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ አይቻልም” ተብሏል።
ረቡዕ ሐምሌ 24 2016 (አዲስ ማለዳ)በማክሮኢኮኖሚው ሳቢያ “ለሚመጣው ምስቅልቅል”፤ መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ኢዜማ ገልጿል።
መንግስት “በገበያ ላይ የተመሰረተ” የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ፤ በሀገር እና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም “የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል” ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው መንግስት እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
ኢዜማ በዚሁ መግለጫው የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ አጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገትን በሚመለከቱ ጉዳዮች “መንግስት በቀጥታ እና በንቁ ሁኔታ ጣልቃ መግባት ካልቻለ፤ “ከጥልቅ ድህነት መውጣትም ሆነ ማህበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ እንደማይቻል” በጽኑ እንደሚያምን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የገባበትን “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት” እና “አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት አጣብቂኝ” “እረዳለሁ” ያለው ፓርቲው፤ ሆኖም መንግስት ለችግሮቹ የወሰደውን መፍትሔ ተችቷል።
የአምራች ዘርፉ “እንጭጭ በሆነ” እና ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ “ጥገኛ ለሆነች ሀገር” መንግስት የተከተለው መፍትሔ፤ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪን በማስከተል “የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያባብስ” መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል።



