በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 26 ማረሚያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ የጥራት እና የንጽህና ጉድለት እንዳለባቸው ተገለጸ    

0
422

ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ የሰባዓዊ መብቶች ጉባኤ ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 26 ማረሚያ ቤቶች እና 51 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባደረገው ክትትል ወጥ የሆነ የፖሊስ ጣቢያ ግንባታ መለኪያ አለመኖር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የጥራት ጉድለት ያለባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢሰመጉ ዛሬ ባወጣው ባለ 76 ገጽ ሪፖርት ላይ አዲስ አበባ ጨምሮ በ9 ክልሎች አስተዳደር ስር የሚገኙ ማረሚያ ቤቶችን እና ፖሊስ ጣቢያዎችን እንደጎበኘ ገልጧል፡፡

ተቋሙ በሁለት ዙር አደረኩት ባለው በዚሁ ማጣራት በማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያዎቸ ክፍሎቻቸው ንፅህናቸውን ያልጠበቁ፣ ጠባብና የተጨናነቁ ለተጠርጣሪዎች ማቆያነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ፍራሽ፣ አልጋ፣ አንሶላ፣ ብርድልብስ፣ የንፅህና መጠበቂያ ያልተሟላላቸው መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

እንዲሁም በአብዘኛው ፖሊስ ጣቢያ የምግብ አቅርቦት፣ የታዳጊ ተጠርጣሪዎች የተለየ ክፍል፣ ፖሊስ ጣቢያው ለተጠርጣሪዎች የሚሆን የህክምና ክፍል እንደሌላቸው ተገልጻል፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሚገቡበት ጊዜ መብትና ግዴታቸው እንደማይነገራቸው፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለቤተሰቦቻቸውም እንዲያሳውቁ እድል እንደማይሰጣቸው፣ አብዛኞቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልሆነም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች ኢ-ሰብዓዊ እና ጭካኔ የተሞላበት አያያዝ እንደ ዲሲፕሊን ቅጣትና መረጃ መሰብሰቢያ መንገድ ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ ተጠርጣሪዎችን በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የአደራ እስረኛ ናቸው በሚል ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እና ያለ ክስ፣ ያለ ውሳኔ ምንም አይነት የምግብ አቅርቦት በሌለበት ፖሊስ ጣቢያ ለረጅም ጊዜ ታስረው የሚገኙ ሰዎች እንዳሉ ኢሰመጉ ከተጠርጣሪዎች እና ከፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች ካሰባሰበው መረጃ ለማወቅ መቻሉን አስታውቋል፡፡

ይህን ተከትሎም ኢሰመጉ በየክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የምግብ አቅርቦትና ጥራት ችግር፣ ህክምና የማግኘት ችግር፣ የመኝታ አልጋዎችና የአልባሳት ችግር፣ አቅም በፈቀደ መጠን እንዲስተካከሉ አሳስቧል፡፡

በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ኢሞራላዊ እና ከኢትዮጵያዊ ስነምግባር ውጪ የሆኑ ልምምዶች እየተንሰራፉ በመሆኑ ማረሚያ ቤቶች ይህንን ድርጊት እንዲቆጣጠሩ አስጠንቅቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here